ቦርዱ የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ባወጣው መመሪያ ላይ የሕዝብ አስተያየት ለመቀበል ጥሪ አደረገ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቀጣይ በሚደረገው 6ኛ አገራዊ ምርጫ ሂደት ወቅት የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ባወጣው መመሪያ ላይ የሕዝብ አስተያየት ለመቀበል ጥሪ አድርጓል።

የመመሪያው ዋና ዓላማ በምርጫ ሂደት ወቅት የኮቪድ 19 ስርጭትን መከላከል እና መቆጣጠር በቅድመ ምርጫ፣ በድምፅ መስጫ ቀን እና በድኅረ ምርጫ ወቅት ከምርጫ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ተግባራት ሁሉ የኮቪድ-19 ስርጭትን እንዳይጨምሩ ማድረግ መሆኑንም ገልጿል።

ለቦርዱ እና ለምርጫ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ለምርጫ አስፈጻሚ አካላት በሙሉ ሊሟሉላቸው የሚገቡ ሁሉም የኮቪድ-19 አስፈላጊ መስፈርቶች የረቂቅ መመሪያው የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን አስታውቋል።

በመሆኑም ረቂቅ መመሪያው ላይ አስተያየት ያላቸው አካላት ከታኅሣሥ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በlegal@nebe.org የኢ-ሜይል አድራሻ እንዲሁም በድረ ገጹ መልእክት ማስቀመጫ አማካኝነት ለቦርዱ የሕግ ክፍል እንዲልኩ ጥሪ ማቅረቡን ከቦርዱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።