“ቪዛ በማንኛውም ስፍራ” የተሰኘ ኢኒሽየቲቭ ተግባራዊ ሊደረግ ነው

ግንቦት 01/2013 (ዋልታ) – የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ዓለም አቀፉ የክፍያ ቴክኖሎጂ ተቋም (ቪዛ) ዲጂታይዜሽንን ለማሳለጥ እንዲሁም የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ድርጅቶችን ለመደገፍ “ቪዛ በማንኛውም ስፍራ” የተሰኘ ኢኒሽየቲቭ ተግባራዊ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡
የኢኖቬሽና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ (ዶክተር) የኢትዮጵያ መንግሥት አካታች የፋናንስ ሥርዓትን ለመገንባት ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ያምናል፤ ይህንን እውን ለማድረግም “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” የተሰኘ ስትራቴጂ መቅረፁን ተናግረዋል፡፡
ስትራቴጂው ለሕዝብ፣ ለመንግሥትና ለንግዱ ማኅበረሰብ የክፍያ ሥርዓቶች በስፋት ለማቅረብ የሚያስችልና ዲጂታይዜሽንን እንደ ቁልፍ እርምጃ ያስቀመጠና ግቡም አድርጎ የወሰደ ነው ብለዋል፡፡
የቪዛ ምክትል ፕሬዘዳንትና ከሰሃራ በታች ላሉ ሀገሮች የድርጅቱ ኃላፊ አይዳ ዲያራ “ይህ አጋርነት ድርጅታችን ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ያለውን ቁርጠኝነት በጉልህ የሚያሳይ ነው” ብለዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ለፋይናንስ ቴክኖሎጂ ተቋማት አስቻይ ሥርዓትን ለመገንባት በትክክለኛ መንገድ እየተጓዘች ነው ያሉት ኀላፊዋ ቪዛ በሁሉም ስፍራ ገንዘብ ማስተላለፍ እንዲኖር መፍትሔ ለሚያበጁ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ድርጅቶች ያልተቋረጠ ድጋፍ መስጠት ዋነኛ ግባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቪዛ በተናጠል በአዲስ አበባ የሚገኝ የዲጂታል ሚዲያና ዳታ፣ በኢኖቬሽን፣ ቴክኖሎጂና ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ዙርያ በትኩረት የሚሠራ ሸጋ ሚዲያና ቴክኖሎጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በጋራ በመሆን “ቪዛ በማንኛውም ስፍራ 2021” የተሰኘውን ፕሮግራም ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ቪዛ ስልጠና በመስጠት፣ በአቅም ግንባታ ሥራዎች፣ በሀገሪቱ ያሉ የዲጂታይዜሽን እድሎችን የመለየትና የመፈተሸ ሥራ በጋራ ሲሠሩ፤ ሸጋ ሚዲያና ቴክኖሎጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር “ቪዛ በማንኛውም ስፍራ 2021” የተሰኘውን ፕሮግራም ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ላይ የሚሳተፍ ይሆናል ተብሏል።
(ምንጭ:- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር)