ተመራማሪዎች የዲጂታል አሰራሮች ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ የካቲት 12/2013(ኢዜአ)- የኢትዮጵያ ስትራቴጂክ ጉዳዮች ጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች የዲጂታል አሰራሮች ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

ሚኒስቴርሩ  ለኢትዮጵያ ስትራቴጂክ ጉዳዮች ጥናት ኢንስቲትዩት አዲስ ተቀጣሪ ተመራማሪዎች ስለ ዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ገለፃ አድርጓል።

ገለፃው እንደ ስትራቴጂክ ጥናት ተመራማሪ ስለ አለም-ዓቀፍ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ማወቅ ያለባቸው ክህሎቶች ላይ መነሻ የሚሆን ሃሳብ ለማስጨበጥ ያለመ መሆኑም ተገልጿል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሀመድ (ፒ ኤች ዲ)  ባደረጉት ገለጻ  ተመራማሪዎቹ ለዲጂታል አሰራር ትኩረት በመስጠት ለኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ዝርዝር ቴክኒካል ስልጠናዎችንም በቀጣይ በተከታታይ ለመስጠት መታቀዱን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል አሰራሮችን በመተግበር የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት እየሰራ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።