የአውሮፓ ሕብረት በአፍሪካ ክትባቶችን ተደራሽ ለማድረግ 100 ሚሊዮን ዩሮ መደበ

የካቲት 12/ 2013(ዋልታ) – በአፍሪካ የኮቪድ-19 እና የሌሎች በሽታዎች ክትባቶችን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ 100 ሚሊዮን ዩሮ መድቦ እየሰራ መሆኑን የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

በዚህም በአፍሪካ ክትባቱን የሚያመርቱ ኩባንያዎችን አቅም ለማጎልበት እንሰራለን ሲሉ የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል፡፡

ይህም አሁን ላይ የኮቪድ-19 ክትባትን ተደራሽ ለማድረግና ወደፊት ለሚከሰቱ ወረርሽኞች ክትባት ለማዘጋጀት አቅም የሚፈጥር እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

የገንዘብ ድጋፉ በአፍሪካ የበሽታ መከላከያና መቆጣጠርያ ማዕከል በኩል የአገራትን የጤና ስርዓት ለማጠናከር፣ ለባለሞያዎች ስልጠና ለመስጠት፣ የሕክምና መሳሪያዎችን ለመግዛት እና መሰል እገዛ ለማድረግ የሚውል ነው ተብሏል፡፡

በቡድን 7 የታላላቅ ሀገራት አደረጃጀት በኩል እንደተገለጸው የአውሮፓ ሕብረት በዓለም አቀፍ ደረጃ የክትባትን ፍትሃዊ ተደራሽነት ለማረጋገጥ ለሚሰራውና ኮቫክስ ለተሰኘው ተቋም የሚያደርገውን ድጋፍ የሚያደርገውን ድጋፍ ከ500 ሚሊዮን ዩሮ ወደ 1 ቢሊዮን በእጥፍ ማሳደጉንም ፕሬዚዳንቷ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

“ደህንነታችን የሚረጋገጠው የመላው ዓለም ደህንነት ሲጠበቅ ነው” ያሉት መዝ ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን በዚህ አዲስ የገንዘብ ድጋፍ ክትባቶች በቅርቡ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው አገራት እንዲደርሱ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡