ተቋሙ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ስርዓትን ለመተግበር እየሰራ ያለው ስራ በመጠናቀቅ ላይ ነው

ግንቦት 23/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ስርዓትን ለመተግበር እየሰራ ያለውን ስራ በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡
በተቋሙ የንብረት ዋጋ ክለሳና አይ ኤፍ አር ኤስ ትግበራ ፕሮጀክት መምሪያ ስራ አስኪያጅ አቶ ይርጉ ኃይሉ እንዳስታወቁት፣ ተቋሙ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ስርዓትን ለመተግበር ፌር ፋክስ እና ፒ ደብሊው ሲ ከተሰኙ ሁለት ኩባንያዎች ጋር ስምምነት በማድረግ ወደ ስራ ገብቷል፡፡
በአሁኑ ሰዓትም የንብረት ቆጠራውን መረጃ የመሰብሰብና ወደ ገንዘብ የተመን የዋጋ ክለሳ ስራ ተጠናቋል ብለዋል፡፡
የ24 ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች፣ 129 ማከፋፈያ ጣቢያዎች፣ 36 ሺህ 210 የኃይል ተሸካሚ ምሶሶዎች፣ 9 መቶ 48 ተሽከርካሪዎችንና ማሽነሪዎች፣ 48 ሺህ የቤትና የቢሮ ዕቃዎችን እንዲሁም የ3 ሺህ 232 ህንፃዎች የዋጋ ትመና ስራ መከናወኑንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በቆጠራው የተካተቱ ንብረቶች ወደ ገንዘብ ሲተመኑ የተቋሙ ሀብት 382 ቢሊየን ብር እንደደረሰ አቶ ይርጉ አስታውቀዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለፃ የቆጠራና የትመና ስራው የተከናወነው እ.ኤ.አ. በ2016 እና ከዚህ በፊት አገልግሎት በመስጠት ላይ በነበሩት ንብረቶች ላይ በተካሄደ የአይ ኤፍ አር ኤስ ስራና የንብረት ክለሳ ስራ በመስራት ሲሆን፣ የዋጋ ትመናው የገናሌ ዳዋ 3፣ የረጲ ከደረቅ ቆሻሻ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ እና በግንባታ ላይ ያሉትን ግዙፍ ፕሮጀክቶች አላጠቃለለም፡፡

ተቋሙ ፌር ፋክስ ከተሰኘ ኩባንያ ጋር ያሉትን ንብረቶች ለመቁጠርና የዋጋ ክለሳ ስራዎችን ለማከናወን የ2 ነጥብ 8 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ስምምነት ተፈርሞ እንደነበር ያስታወሱት ስራ አስኪያጁ፣ ኩባንያው በውሉ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ስራውን ባለመፈፀሙ ተጨማሪ የጊዜ ማራዘሚያ ተሰጥቶት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለፃ ፌር ፋክስ በአሁኑ ወቅት ከማጠናቀቂያ ስራዎች በስተቀር የተሰጠውን ስራ በውሉ መሰረት ያከናወነ ሲሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት የተደረገለት የውል ማራዘሚያም ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ አለመደረጉን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡