በደቡብ እና ሲዳማ ክልሎች ተምች መከሰቱን የየክልሎቹ የግብርና ቢሮዎች አስታወቁ

ግንቦት 23/2013(ዋልታ) – የደቡብ ክልል የግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ዳምጠው እንደገለጹት፣ በደቡብ ክልል ሁለት አይነት ተምች ተከስቷል።

አንደኛው መጤ እና ከዚህ በፊትም ተከስቶ የነበረ ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ “አፍሪካን አርሚ ዎርም “የሚባል ሲሆን መደበኛና በመንጋ በመሄድ ሳርን የሚመገብና ከባድ ጥፋትም የሚያስከትል የተምች አይነት መሆኑን ጠቁመው ፣ መጤው ተምች የአገዳ ሰብሎች ላይ በተለይ ደግሞ በቆሎና ማሽላን ያጠቃል ብለዋል።

ተምቹ በሰባት ዞንና በአንድ ልዩ ወረዳ ላይ ተከስቷል ያሉት ኃላፊው፣ እስካሁን ድረስ በ321 ቀበሌዎች 34 ሽህ አንድ መቶ ሄክታርን አዳርሷል። ከዚህ ውስጥ 18 ሺህ ሄክታሩን በባህላዊ መንገድ የመከላከል ስራ እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።

ቀሪውን በከፍተኛ ደረጃ በጨፈቃና በእጅ በመግደል የመከላከል ስራዎች እየተከናወኑ ነው። እንዲሁም የኬሚካል አቅርቦትንና ሕዝቡን በቅንጅት በማስተባበር የመምራት ሥራዎች ተጠናክረው እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በጊዜው መከላከል ካልተቻለ የጉዳት መጠኑ ከፍ ያለ ነው ያሉት ኃላፊው፣ በተለይ “የአፍሪካ አርሚ ዎርም” በመባል የሚወቀው መቶ በመቶ ሰብል ላይ ጉዳት ያደርሳል።መጤው ተምችም ቢሆን በከፍተኛ ደረጃ ከ50 በመቶ በላይ የምርት መቀነስ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ብለዋል፡፡

የሲዳማ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ መስፍን ቃሬ በበኩላቸው ፣ ተምች በሲዳማ ክልል በያዝነው ሳምንት ከማክሰኞ ጀምሮ በአንድ አንድ አካባቢዎች ታይቷል።

በተደረገው ማጣራት በሰባት ወረዳዎች ላይ መከሰቱን እንዳስታወቁ ኢፕድ ዘግቧል።