ታላቁ ሩጫ የአገራችንን ገጽታ ገንብቷል – ም/ ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሩጫና ከስፖርትነት ባለፈ የአብሮነት፣ የስኬት፣ የፍቅር እንዲሁም የቱሪስት መስህብ በመሆን የኢትዮጵያን ገጽታ መገንባቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

20ኛውን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ያስጀመሩት ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች እንዳሉት÷ እንደወትሮዉ ሁሉ በድምቀት፣ አዝናኝ እና አስደሳች በሆነ መልክ በከተማችን እየተካሄደ ይገኛል።

እኛም እንደሩጫው ሁሉ አገራችን በምታደርገው ድህነትን የማሸነፍ፣ ዘላቂ እድገትን የማስመዝገብ እና የታላቅነት ጉዞ በየእለት ኑሮአችን አሸናፊዎች እንሁን ሲሉ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሴክሬታሪ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።

በውድድሩ አቤ ጋሻሁን በወንዶች እንዲሁም ፅጌ ገ/ሰላማ በሴቶች አሸናፊ ሆነዋል።

የ20ኛው የ2013 ዓ.ም የታላቁ ሩጫ የወንዶች አሸናፊዎች ፦

1ኛ. አቤ ጋሻሁን – ከአማራ ማረሚያ

2ኛ. ታደሰ ወርቁ – ደቡብ ፓሊስ

3ኛ. ሚልኬሳ መንገሻ – ከሰበታ ክለብ

የ20ኛው የ2013 ዓ.ም የታላቁ ሩጫ የሴቶች አሸናፊዎች ፦

1ኛ. ፅጌ ገ/ሰላማ – ከኢትዮ አትሌትክስ

2ኛ. መድን ገ/ስላሴ  – ከንግድ ባንክ

3ኛ. ገበያነሽ አያሌው – ከመከላከያ