የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና ውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በበይነ መረብ ስብሰባ አካሄዱ

የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን  የውጭ ጉዳይ እና ውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዛሬው ዕለት በበይነ መረብ ስብሰባ አካሂደዋል።

ስብሰባው በደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት አስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሰብሳቢነት ተካሂዷል።

ሚኒስትሮቹ የሕዳሴ ግድብ ድርድር በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ምክክር አድርገዋል።

ስብሰባው ባሳለፍነው ሳምንት እንዲካሄድ ስምምነት ተደርሶበት የነበረውን የሦስትዮሽ ስብሰባ ላይ ሱዳን ባለመገኘቷ ምክንያት ከቀረ በኋላ የተካሄደ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

በስብሰባው ላይ የአፍሪካ ኅብረት አስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀመንበር ድርድሩን ለማስቀጠል ይረዳል በሚል አገራቱ ለሦስት ቀናት ለአፍሪካ ኅብረት ባለሞያዎች ጋር የሁለትዮሽ ስብሰባ እንዲያካሂዱ፣ በማስከተል የሦስትዮሽ ስብሰባ እንዲካሄድ እና ውጤቱ ለሊቀመንበሯ እንዲገልጽ ሐሳብ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ እና ግብጽ ይህንን ተቀብለው ለመቀጠል የተስማሙ ሲሆን፣ ሱዳን ሐሳቡን ባለመቀበሏ ስብሰባው በዚሁ መጠናቀቁን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ኢትዮጵያ የሱዳን ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዲቻል በግድብ ደህንነት፣ በመረጃ ልውውጥ እንዲሁም በሌሎች ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።