ትዊተር በአፍሪካ ያሉትን ሰራተኞች ቀነሰ

ትዊተር

ኅዳር 1/2015 (ዋልታ) ትዊተር የአፍሪካ ብቸኛ መቀመጫ በሆነው በጋና በሚገኘው ቢሮው ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞችን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ መቀነሱ ተገለጸ።

ተቋሙ ወጪውን ለመቀነስ በማሰቡ መዋቅሩን በድጋሚ እያጤነ እንደሚገኝ የሚገልጽ ኤሜይል ለሰራተኞቹ መላኩን ቢቢሲ እንደተመለከተ ዘግቧል፡፡

ትዊተርን በቅርቡ የገዛው ባለቤቱ ኤሎን መስክ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰራተኛ ቅነሳ እንዲደረግ መወሰኑ ይታወሳል።

የጋናው ቢሮ ባለፈው ዓመት የተከፈተ ሲሆን ለተቀነሱት ሰራተኞች ምንም አይነት የካሳ ክፍያ እንዳልቀረበና ይልቁንም ደመወዛቸው ውላቸው እስከሚያልቅ ድረስ ይከፈላቸዋል መባሉን ቢቢሲ ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ አመላክቷል፡፡ ይህም እስከሚቀጥለው ወር ድረስ እንደሆነም ጠቅሷል።

ከአንድ ሳምንት በፊት ኤሎን መስክ ለሚቀነሱ ሰራተኞች የሦስት ወር ደመወዛቸው በካሳ መልኩ እንደሚከፈላቸው የገለጸ ቢሆንም ስለየትኛው የትዊተር ቢሮ ለመግለጽ እንደፈለገ ግልጽ አላደረገም።

የትዊተር አዲሱ ባለቤት መስክ ሰራተኞችን ከመቀነስ ውጪ ሌላ አማራጭ የለኝም ሲሉ ተናግረዋል። ለዚህም እንደ ምክንያት ያቀረቡት ድርጅታቸው በቀን ከ4 ሚሊዮን ዶላር በላይ እያጣ መሆኑ ነው።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW