ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ህግ የማስከበር ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠሉን መንግሥት አስታወቀ

ለገሰ ቱሉ (ፒኤችዲ)

ሰኔ 23/2014 (ዋልታ) ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ህግ የማስከበር ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠሉን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ፒኤችዲ) የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫና ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ህግ የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል።

በተወሰደው ህግ የማስከበር ዘመቻ ተሳታፊ የነበሩ ህገ ወጦች በቁጥጥር ስር እንደዋሉም አስታውቀዋል።

በተከናወነው የህግ ማስከበር ሥራ በ100 ሚሊዮን የሚቆጠሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ገንዘቦች መያዛቸውንም ተናግረዋል።

በኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ክልል የተፈፀመው ንጹሃን ግድያ አስነዋሪ ድርጊት መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ የሽብር ቡድኑ ላይ የተወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን አመላክቷል፡፡

ንፁሃን ዜጎች ላይ ኢላማ ያደረገውን የሽብር ቡድኖች ድርጊት ለመከላከል ኅብረተሰቡ ሳይከፋፈል ኅብረ ብሔራዊ አንድነቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው በመግለጫው የተመላከተው።

መጪው ጊዜ የሕዳሴ ግድብ የሚሞላበትና ኃይል የሚያመነጭበት እንደመሆኑ ኅብረተሰቡ ሀገሩንና አካባቢውን የመጠበቅ ሥራውን ማጠናከር ይኖርበታል ተብሏል። የሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌቱም በተያዘለት ቀነ ገደብ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

መንግሥት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ከሐምሌ 2013 እስከ ሰኔ 2014 ዓ.ም ድረስ በርካታ የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የገለጹት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ወደ ትግራይ ክልል የሚገባው ድጋፍ በአግባቡ ለኅብረተሰቡ እየደረሰ እንዳልሆነም ጠቁመዋል፡፡

ለአማራና ለአፋር የሚገባው የሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉንም በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡

በምዕራብ ወለጋ ለተጎዱ ዜጎች እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደቀጠለ እንዲሁም በድርቅ ለተጎዱ ዜጎችም እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉ በመግለጫው ተመላክቷል።

ኢኮኖሚ ላይ የሚታዩ ፈተናዎችን ለመቅረፍ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የተገለፀ ሲሆን በክረምት ወቅትም የከተማ ግብርና ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል።

በክረምት ወራት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የአቅመ ደካሞችን ቤት ለማደስ በትኩረት እንደሚሰራም በመግለጫው ተጠቁሟል።

መንግሥት ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት ፍላጎት እንዳለው በተደጋጋሚ ቢያስታውቅም የሽብር ቡድኑ ሕወሓት ለሰላም ያለው ቦታ አናሳ እንደሆነ ማሳየቱም ተገልጿል።

በሱራፌል መንግሥቴ

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW