ኒጀር የፈረንሳይ ወታደሮችን በአስቸኳይ ለማስወጣት ንግግር ስለመጀመሯ ተሰምቷል

ነሐሴ 30/2015 (አዲስ ዋልታ) አዲሱ የኒጀር ወታደራዊ መንግስት የፈረንሳይ ወታደሮችን ከሀገሪቱ ለማስወጣት ንግግር መጀመሩን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አሊ መሃማን ላሚን ዘይኔ ገለጹ።

የኒጀር ወታደራዊ መንግስት መሪ ጄኔራል አብዱራህማን ቲቺያኒ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው የሾሟቸው አሊ መሃማን ላሚን ዘይኔ ይህን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች ሰፋ ያለ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ከምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ECOWAS) ጋር ንግግር መቀጠሉን አመላክተዋል።

በዚህም ኢኮዋስ በኒጀር ላይ የጣለውን ማዕቀብ በተቻለ ፍጥነት ለማስነሳት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየተነጋገሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

ንግግሩም ፍሬ አፍርቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከስምምነት ላይ እንደምንደርስ ተስፋ እናደርጋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም የኒጀር ወታደራዊ መንግስት ከፈረንሳይ ጋር በመነጋገር የፈረንሳይ ወታደሮች ከምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር በፍጥነት ለቀው እንዲወጡ የሚያስችል ድርድሮች በመካሄድ ላይ እንደሆኑ ጠቁመዋል።

የፈረንሳይ ወታደሮች በኒጀር እንዲገኙ የሚፈቅደውን ስምምነት በወታደራዊው መንግስት መሰረዙ የሚታወስ ነው።

ይህን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእነሱ በግዛታችን መገኘት ህገወጥ ነው ያሉ ሲሆን በዚህም ሀገሪቱን በፍጥነት ለቀው እንዲወጡ እየተነጋገሩ መሆናቸውን አናዶሉ ዘግቧል።

ከጥቂት ቀናት በፊት በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በኒጀር ዋና ከተማ የፈረንሳይ ወታደሮች በምዕራብ አፍሪካ ሀገር መኖራቸውን ተቃውመው ሰልፍ መውጣታቸው ይታወሳል።