አመታዊው የቁልቢ ገብርኤል ንግስ በዓል በሰላም ተከብሯል – ፖሊስ

ሐምሌ 192013 (ዋልታ) – አመታዊው የቁልቢ ገብርኤል ንግስ በዓል ዛሬ በሰላም መከበሩን ፖሊስ አስታወቀ።
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ድቪዥን ክፍል ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ቶሎሳ ጎሹ ለኢዜአ እንደገለጹት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኦርቶዶክስ ሀይማኖት ተከታዮች የታደሙበት አመታዊው የቁልቢ ገብርኤል ንግስ በዓል ያለ ጸጥታ ችግር በሰላም ተከብሯል።
በአካባቢው የተቋቋመው የጸጥታ አካል ባካሄደው አስቀድሞ የወንጀል መከላከል ስራና ህብረተሰቡ በመገናኛ ብዙሀንና በተለያዩ ዘዴዎች የተሰጠውን መልዕክት ተቀብሎ ባደረገው ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ በዓሉ በሰላም ሊከበር መቻሉን ተናግረዋል።
ወጣቶችን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች ለምዕመናን ያደረጓቸው አቀባበልና የመስተንግዶ ስነ ስርዓት በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ጉልህ አስተዋፅኦ ማድረጉን አመልክተዋል።
በንግስ በዓሉ የተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ሰርቀው እጅ ከፍጅ የተያዙ አምስት ግለሰቦች በበዓሉ ስፍራ በተቋቅመ ጊዜያዊ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው በምርመራ ተጣርቶ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ መደረጉን ኢዜአ ዘግቧል።
ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮቹ ለተሰረቁባቸው ባለንብረቶች እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል።
ምዕመናኑ ወደ ንግስ በዓሉ መምጣት ከጀመሩበት ከባለፈው አርብ ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ ምንም ዓይነት የተሽከርካሪ አደጋም ሆነ ግጭት አለመድረሱን አመልክተዋል።
ምእመናን ከበዓሉ በኋላ ወደየ አካባቢያቸው ሲመለሱ ከዚህ ቀደም ያሳዩትን የትራፊክ ህግ ስነስርዓት አከባበር እንዲደግሙ ዋና ኢኒስፔክተሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።