አሜሪካ በሌሎች ሀገራት የምታደርገውን ጣልቃ ገብነት እንድታቆም ቻይና አሳሰበች

ግንቦት 19/2013 (ዋልታ) – አሜሪካ በሌሎች ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ የምታደርገውን ጣልቃ ገብነት እንድታቆም ቻይና አሳሰበች፡፡
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዣኦ ሊጂያን በሰጡት መግለጫ አሜሪካ የሀሰት መረጃ ከማሰራጨት እንድትቆጠብ እና በራሷ የውስጥ ጉዳዮች ላይ እንድታተኩር አሳሰበዋል።
በፍሎይድ የፍርድ ሂደት ባሉት 21 ቀናት ውስጥ ብቻ በአሜሪካ 64 ሰዎች በፖሊስ በጥይት የተገደሉ መሆናቸውን መረጃዎች እንደሚያመለክቱ የገለጹት ዣኦ፣ እነዚህ ከተገደሉ ሰዎች አብዛኛዎቹ የቆዳ ቀለማቸው የተለየ መሆኑን ተናግረዋል።
በህዝብ አስተያየት ጥናት መሠረት ባለፉት ዓመታት በአፍሪካ-አሜሪካውያን እና በአሜሪካ ፖሊሶች መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ከፋ ቀውስ እየተሸጋገረ መሆኑን ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት።
72 በመቶ የሚሆኑት አፍሪካ-አሜሪካዊያን በሰጡት መልስ ወጣት አፍሪካ-አሜሪካውያንን እና ሌሎች አናሳ የህብረተሰብ ክፍሎች በፖሊስ የሚደረገው ተኩሶ መግደል እየተባባሰ መምጣቱን ተናግረዋል።
አሜሪካ በራሷ ጉዳይ ላይ እንድታተኩር፣ የራሷን ችግሮች እንድትፈታ፣ የዜጎቿን ደህንነት እንድትጠብቅ እንዲሁም በነጻነት እንዲተነፍሱ እና ከፍርሃትና አድልዎ የመላቀቅ መብት እንዲሰጣቸውም አሳስበዋል ሲል የዘገበው ሺንዋ ነው።