መጋቢት 6/2015 (ዋልታ) አሜሪካ በፈረንጆቹ 2023 በኢትዮጵያ ለሰብአዊ ዕርዳታ የሚውል የ331 ሚሊዮን ዶላር አዲስ ድጋፍ እንደምታደርግ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን አስታወቁ።
ለአንድ ቀን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የሚገኙት አንቶኒ ብሊንከን በሰጡት መግለጫ ድጋፉ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) በኩል እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን አሜሪካን ግቢ የሚገኘውን የመጀመሪያውን የአሜሪካ ኤምባሲ ቆንስላ ጽሕፈት ቤትን ጎብኝተዋል።
አሜሪካን ግቢ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ አንፀው ይኖሩበት እንደነበር ይታወቃል፡፡
በ1930 ዎቹ የአሜሪካ ኤምባሲ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ሆኖ ማገልገሉም ይታወሳል፡፡ በኋላም የየመን ኮሚኒቲ ትምህርት ቤት ሆኖ ሲያገለግል እንደነበር ተገልጿል፡፡
የአሜሪካ ኤምባሲ ከዓለም ቅርሶች ፈንድ ጋር በመተባበር በአሜሪካ ግቢ የሚገኘውን በፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ የታነፀ ታሪካዊ ሕንፃ አድሶ ማስመረቁን ኢፕድ ዘግቧል፡፡