አሜሪካ በኮቪድ ክትባቶች ላይ የአዕምሯዊ መብት ጥበቃ እንዲነሳ ድጋፍ ሰጠች

ክትባቶች ላይ የአዕምሯዊ መብት ጥበቃ

ሚያዝያ 28/2013 (ዋልታ) – አሜሪካ በዓለም ንግድ ድርጅት መድረክ ላይ በኮቪድ-19 ክትባቶች ላይ የአዕምሯዊ መብት ጥበቃ እንዲነሳ ድጋፍ ሰጠች።

የዓለም ንግድ ድርጅት አባል አገራት ለኮቪድ-19 ክትባቶች የባለቤትነት ጥበቃ እንዳይደረግ ቢስማሙ፤ ደሃ አገራትን ጨምሮ በርካቶች ክትባቶቹን ማምረት እና በዝቅተኛ ዋጋ ለተጠቃሚ ማድረስ ይችላሉ ተብሏል።

ከዚህ ቀደም ሕንድ እና ደቡብ አፍሪካ የክትባት አበልጻጊዎቹ የያዙት የአዕምሯዊ መብት ጥበቃ እንዲነሳ አጥብቀው ሲወተውቱ ቆይተዋል።

ይሁን የእንጂ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አስተዳደር፣ የአውሮፓ ሕብረት እና ዩናይትድ ኪንግደም የክትባቶቹ የአዕምሯዊ መብት መጠበቅ አለበት ሲሉ ቆይተዋል።

መድሃኒት አምራች ኩባንያዎችም የአዕምሯዊ መብት እንዲነሳ መደረጉ የተፈለገውን ውጤት ሊያመጣ አይችልም በሚል የጆ ባይደንን አስተዳደር ትችተዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ውሳኔ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመዋጋት ቁልፍ እርምጃ ነው ብለዋል።

የዚህ ሃሳብ ደጋፊዎች እንደሚሉት፤ በክትባቱ ዙሪያ ያሉ የአዕምሯዊ መብት ጥበቃዎች እንዲነሱ ቢደረግ ክትባቱን በበርካታ ቦታዎች በብዛት ማምረት እና ሚሊየኖችን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል።

አገራት ክትባቱን በአገራቸው እንዳያመርቱ ከመብት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እንቅፋት እንደሆኑባቸውም ሲገልጹ ነበር።

የአሜሪካ የንግድ ተወካይ በዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅት መድረክ ላይ አገራቸው በክትባቶቹ ዙሪያ ያለውን የመብት ጥበቃዎች እንዲነሱ ትወተውታለች ብለዋል።

በክትባቶቹ ዙሪያ ያሉት የመብት ጥበቃዎች የሚነሱት 164 የድርጅቱ አባል አገራት በሙሉ ሲስማሙ ነው ተብሏል።

የክትባት ባለቤት የሆኑ ድርጅቶችን የአዕምሯዊ መብት ለማንሳት ረጅም ጊዜ ሊወስድ እንደሚችልም ተገልጿል።

የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ውሳኔን “አሳዛኝ” ነው ሲል የዓለም የመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ማህበር ገልጾታል። ማህበሩ “የአምራቾችን መብት ማንሳት ውስብስብ ለሆነ ችግር ትክክል ያልሆነ መልስ መስጠት ነው” ብሏል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።