መጋቢት 18/2016 (አዲስ ዋልታ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በሁለትዮሽ ግንኙነት እና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የግጭት እና ማረጋጋት ሥራዎች ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ኤን ዊኮክሲ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸው ወቅት አምባሳደር ምስጋኑ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት እና ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ለማስፋት የሁለትዮሽ ግንኙነትን መገምገም ያለውን ጠቀሜታ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የጋራ መግባባትን በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግና በትግራይ ክልል መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባትና የመልሶ ማቋቋም ሥራን እውን ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡
በግጭት የተጎዱ ዜጎችን ለመርዳትና ለማቋቋም መንግስት ፍላጎት እንዳለውም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመው፤ ሰላምን ለማስጠበቅ ለውይይቶች ቅድሚያ መስጠት ወሳኝ ነው ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የግጭት እና ማረጋጋት ሥራዎች ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ኤን ዊኮክሲ በበኩላቸው አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማስፋት ዋጋ እንደምትሰጥ ገልጸዋል።