ሐምሌ 08/2013 (ዋልታ) – የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ሰጥጠዋል፡፡
ባለፉት ስምንት ወራት መንግስት ተገዶ በገባበት የህግ ማስከበር እንቅስቃሴ በዜጎች ህይወት ንብረትና የሀገር ገፅታ ላይ የደረሰው ጉዳት ግዙፍ እንደሆነ ይታወቃል ነው ያሉት፡፡
መንግስት ተጨማሪ ኪሳራንና የህዝብ ጉዳትና እልቂትን ለማስቀረት ሲባል መሰረቱን ሰብአዊነት ላይ ያደረገ ነገር ግን ሌሎችንም ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የሀገር ሉአላዊነት ላይ የተደቀኑ አደጋዎዎችን ግምት ውስጥ ያስገቡና ተያይዥነት ያላቸውን ምክንያቶች ታሳቢ ያደረገ የተናጥል የተኩስ አቁም አውጇል ነው ያሉት፡፡
ይህንንም ተከትሎ ሰራዊቱን ከግጭቱ አከባቢ አስወጥቷል ያሉ ሲሆን በዚህም ምክንያት አታጅቡን አትከተሉን እኛው በተመቸን መንገድ ተንቀሳቅሰን ለብቻችን ሆነን እርዳታ ማድረስ አለብን የሚል ውትወታ ሲያካሄዱ ለነበሩ አካላት እድል ሰጥቷል::
የፍተሻ ኬላዎች ይነሱልን በፍተሸ የሚስተጓጎል ሰዓት አይኑር ምን እንደያዝንም ማንን እንደጫንም ለማወቅ አትሞክሩ ነፃ አድርጋችሁ ልቀቁን በሚል በርካታ ግፊቶችን ሲያካሄዱ ለነበሩ መልስ ሆኗል፤ ግጭቱን ጋብ በማድረግ የተኩስ አቁም ወስኑና ዕርዳታ በቀላሉ ማድረስ የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠር አርሶ አደሩም ይረስ ሲሉ ለነበሩም ምልሽ ሆኗል ነው ያሉት ሚኒስትር ድኤታው፡፡
አዝመራውና የእርሻው ጊዜ ካለፈ ረሀብን እንደመሳሪያ ተጠቅማችሁዋል ብለን እንከሳችኋለንና አዝመራው ሳያልፍ የእርሻው ጊዜ ሳይስተጓጎል ተኩስ አቁማችሁ አርሶ አደሩ ማረስ የሚችልበት ዕድል መፈጠር አለበት የሚል ውትወታ ሲያካሄዱ ለነበሩም ውሳኔው ይጠቅማል፡፡
ዋናው ምክንያታቸው ዋናው መሻታቸው ዋናው ፍላጎታቸው ምንም ይሁን ምን እነዚህን ጉዳዮቻቸውን በተለያዩ የዓለም አደባባዮች በተናጠልም በጋራም ሲያስተጋቡ ለነበሩ አካላት ምላሽ የሚሆን ነበር ተብሎ ይታሰባል ነው ያሉት፡፡