ነሐሴ 13/2013 (ዋልታ) – አሸባሪውን የህወሀት ቡድንን በመደምሰስ የሀገሪቱን ሉአላዊነት ለማስከበር የተጀመረው የድጋፍ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሐረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ -ጉባኤ ወይዘሮ አዲስአለም በዛብህ አስታወቁ።
የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ማካድ ጀምሯል።
አፈ -ጉባኤዋ ወይዘሮ አዲስአለም የጥፋት ቡድኑ የተናጥል ተኩስ አቁሙን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በሀገሪቱ ላይ የሽብር ሴራውን እያካሄደ ነው ብለዋል።
በዚህም በአፋር እና በአማራ ክልሎች ዜጎች ላይ ግድያና ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል፤ ይህን የጥፋት ድርጊት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ያወገዘው ዕኩይ ድርጊት ነው ብለዋል።
ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊትም የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስከበር ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር መሰዋዕትነት እየከፈለ መሆኑን ገልጸዋል።
አሸባሪው የህወሀት ቡድንን በመደምሰስ የሀገሪቱን ሉአላዊነት ለማስከበር የተጀመረው ሁሉን አቀፍ የድጋፍ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው አፈ -ጉባኤ ወይዘሮ አዲስአለም በዛብህ ያስታወቁት።
ጉባኤው ለሶስት ቀናት በሚኖረው ቆይታ የ2013 በጀት ዓመት የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤትና የጠቅላይ ፍርድ ቤት አፈጻጻም ሪፖርት ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተመልክቷል።
እንዲሁም የክልሉ መስተዳድር የ2014 ስራ ዘመን ማስፈጸሚያ በጀት፣ የተለያዩ አዋጆች እና ሹመቶች ላይ በመምከር እንደሚያጸድቅም ይጠበቃል።
በጉባኤው መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት አሸባሪው ህወሃት በአፋር ክልል በዜጎች ላይ በፈጸመው ጥቃት ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት ተካሂዷል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።