ኅዳር 12/2014(ዋልታ) አሸባሪው ሕወሓት በሥልጣን ዘመኑ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ላይ ኢ-ፍትሃዊነት እንዲነግስና ሌብነት እንዲስፋፋ በማድረግ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የባንኩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው ገለጹ፡፡
አሸባሪው ሕወሓት በስልጣን ዘመኑ ልማት ባንክ ላይ ፈርጀ ብዙ ኪሳራዎች ሲያደርስበት እንደነበር የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ በፍትሀዊነት ላይ የሚነሳው ጥያቄ የመጀመሪያ መገለጫው ነው ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ÷ይሰጡ የነበሩ ብድሮች በአግባቡ ያልተመሩ እና የተበላሸ የብድር አመላለስ ሂደቶች የሚስተዋልባቸው ብሎም የማይመለሱ ብድሮች ነበሩ ብለዋል፡፡
ባንኩ በገንዘብ ይደግፋቸው የነበሩ ፕሮጀክቶች በአብዛኛው ወደ አንድ ወገን የሚያተኩሩበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰው፣ ሂደቱም በርካታ ፕሮጀክቶች መድረስ በሚገባቸው ደረጃ ላይ እንዳይደርሱ ተጽዕኖ ፈጥሯል ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
አቅሙና ሐብቱ ያላቸው ክልሎች ላይ ሊተገበሩ ይገባቸው የነበሩ ፕሮጀክቶች ወደ ሌላ አካባቢ የተዘዋወሩበት ሁኔታ እንደነበርም አመላክተዋል፡፡