የስራ ጫና ላለባቸው ሆስፒታሎች ድጋፍ መደረጉ ተገለጸ

ኅዳር 12/2014 (ዋልታ) ከኅልውና ዘመቻው ጋር ተያይዞ የስራ ጫና ላለባቸው ሆስፒታሎች ባለፉት አምስት ወራት ከ474 ሚሊዮን ብር በላይ የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ክልሎች የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በጤና ተደራሽነቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ተፈጥሯል።
ሆኖም ሚኒስቴሩ ችግሮቹን መሰረት ያደረገ የመፍትሄ ሃሳብና የአሰራር ስርአት በመዘርጋት ህዝቡ በተቻለ መጠን የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ከኅልውና ዘመቻው ጋር ተያይዞ የስራ ጫና ላለባቸው ሆስፒታሎች ባለፉት አምስት ወራት ብቻ የህክምና መሳሪያዎችን፣ መድሃኒቶችንና ልዩ ልዩ ገብአቶችን ለማሟላት ከ432 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።
በተጨማሪም በመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች 42 ሚሊዮን ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ሚኒስትሯ ገልጸዋል። በቀጣይም በሁሉም መጠለያ ጣቢያዎች የህክምና ተደራሽነት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ለዚህም ሚኒስቴሩ ከክልሎችና ከተራድኦ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸው ተፈናቃዮች ባሉባቸው አካባቢዎች ጊዜያዊ ጤና ጣቢያዎችን በማቋቋምና ቤት ለቤት የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ የህክምና ቡድኖችን በማዋቀር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የህክምና ባለሙያዎች እስከ ግንባር ድረስ በመዝመት አገልግሎት ከመስጠት ጀምሮ የገንዘብና የደም ልገሳ በማድረግ ጭምር የኅልውና ዘመቻውን በቁርጠኝነት እየደገፉ መሆናቸውን ዶክተር ሊያ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
መደበኛው የህክምና አገልግሎት ሳይቆራረጥ እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡