አሸባሪው ሕወሓት ተስፋ በመቁረጡ ምክንያት ያገኘውን ሁሉ በኢሰብዓዊነት እየጨፈጨፈ ነው – ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ

አወል አርባ

ጥቅምት 12/2014 (ዋልታ) “አሸባሪው ሕወሓት ተስፋ በመቁረጡ ምክንያት ያገኘውን ሁሉ በኢሰብዓዊነት እየጨፈጨፈ ነው” ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ አሸባሪው ሕወሓት በአፋርና አማራ ክልሎች ውስጥ ንጹሐንን መግደሉን፣ ማፈናቀሉና ሀብት ንብረት መዝረፉንና ማውደሙን አስታውሰዋል።

“ቡድኑ ከመንግስት ንብረት በላይ የግለሰቦችን ሀብትና ንብረት እየዘረፈ ያለ ግፈኛ የሽብር ቡድን ነው” ሲሉም የአረመኔነቱን ጥግ ገልጸዋል።

ሊታገዙ እንጂ ሊዘረፉ የማይገባቸውን አቅመ ደካማ አረጋዊያንን እና ማየት የተሳናቸው አካል ጉዳተኞችን ሁሉ ሳይቀር እየዘረፈ ያለ ከሰብዓዊነት የራቀ መሆኑንም አስረድተዋል።

ቡድኑ ከቀድሞው በከፋ መልኩ ከሰብዓዊነት ርቆ የአረመኔነትና የአውሬነት ባህሪ ተላብሶ ያገኘውን ሁሉ በኢ-ሰብዓዊነት እየጨፈጨፈ ያለው ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ስለገባ እንደሆነ አመልክተዋል።

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሸባሪው ሕወሓት አውሬ መሆኑን ተረድቶና ተገንዝቦ ቡድኑን ለመደምሰስ በሚደረገው  እንቅሰቃሴ ግንባር ቀደም ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ቡድኑ ኢትዮጵያን ባስተዳደረበት ወቅት በዙ በደሎችን, ማድረሱን ጠቅሰው፤ ዘረፋና ዜጎችን በማስመረር ለስደት መዳረግ ተግባሩ እንደነበር አስታውሰዋል።

ዘራፊው ቡድን የጊዜ ጉዳይ እንጂ አሁን እየፈፀመ ያለው አረመኔያዊ ድርጊት በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ የሚመከት መሆኑን ገልፀዋል።

‘ታላቋን ትግራይን ለመመስረት ኢትዮጵያ መፍረስ አለባት’ ብሎ ለተነሳው አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያን አደጋ ላይ እንዲጥል የአፋር ህዝብ እንደማይፈቅድለት ገልጸዋል።

ቡድኑ በአፋር ህዝብ የተባበረ ክንድ ኪሳራ እየደረሰበት እንደሚገኝም ርዕሰ መስተዳድሩ መግለፃቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።