አሸባሪው ሕወሓት ወረራ በፈፀሙባቸው አካባቢዎች ከ1 ሺሕ በላይ የጤና ተቋማት መውደማቸው ተገለጸ

ዶክተር ሊያ ታደሰ

ኅዳር 10/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሕወሓትና ግብረአበሮቹ ወረራ በፈፀሙባቸው አካባቢዎች ከ1 ሺሕ በላይ የጤና ተቋማት መዘረፋቸውንና መውደማቸውን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ አንፃራዊ ሠላም በሰፈነባቸው አካባቢዎች የሚገኙ 20 የጤና ተቋማትን በድጋሚ ስራ ማስጀመር የሚያስችል ግብዓት መላኩንም አስታውቋል።

የሽብር ቡድኑ ዓላማ ሕዝብን መጉዳት በመሆኑ እናቶች የሚወልዱባቸውን፣ ሕፃናት የሚታከሙባቸውን የጤና ተቋማት በማውደም ክፋቱን በተግባር አሳይቷል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አሸባሪ ቡድኑ በጤና ተቋማቱ ላይ ከፍተኛ ዝርፊያ በመፈጸሙና የሕክምና ቁሳቁስ በመውደማቸው በርካታ ዜጎች ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

በቡድኑ ወረራ ከተፈጸመባቸው የአማራና የአፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በተጨማሪ የጸጥታ ችግር ባለባቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎችም በተመሳሳይ በጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ጠቁመዋል።

በተደረገው ማጣራት በጤና ጣቢያ ደረጃ ብቻ ከ1 ሺሕ በላይ የጤና ተቋማት ተዘርፈዋል፤ ውድመትም ደርሶባቸዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።