አሸባሪው ሸኔ በጮቢ ወረዳ ቤተክርስቲያንን ጨምሮ ከ178 ሚሊዮን ብር በላይ ንብረትን ሲያወድም 35 የቡድኑ አባላት ተደመሰሱ

ጥር 4/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሸኔ በምዕራብ ሸዋ ዞን ጮቢ ወረዳ ቤተእምነትን ጨምሮ ከ178 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የመንግሥትና የግል ንብረት አወደመ።

አሸባሪው ቡድን ቤተእምነትን ጨምሮ ትምህርት ቤት፣ አንቡላንሶች፣ የሚሊሻ ቤቶች እና ሌሎች የመንግሥት ተቋማት ላይ ጥቃት በማድረስ ሙሉ በሙሉ ማውደሙን የወረዳው አስተዳደርና ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ጀልቀባ ጨቀሳ ለዋልታ ገልፀዋል።

የሽብር ቡድኑ በምዕራብ ሸዋ ዞን ሀገረ ስብከት በጮቢ ወረዳ የጮቢ ደብረ መድኃኒት መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን ሙሉ በሙሉ አውድሟል።

የቤተ ክርስቲያኑ ሰበካ ጉባኤ አባላት ለዋልታ እንደገለፁት ከሆነ  ቤተ እምነቱ ከ150 ዓመት በላይ እድሜ የነበረው ነው። በከተማው የሚኖሩ የእምነቱ ተከታዮች ለዘመናት ይገለገሉበት የነበረ ቅዱስ ስፍራ እንደነበረም ነው ያስረዱት።

የሽብር ቡድኑ ቤተ እምነትን ሳይቀር በማቃጠል አረመኔያዊና ጭካኔ የተሞላበት ተግባር በመፈፀም ፀረ ሕዝብነቱን በግልፅ አሳይቷል ነው ያሉት።

የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊው በበኩላቸው በከተማዋ የሚገኙ የጤና ተቋማት፣ አምቡላንስና ትምህርት ቤት ጨምሮ የሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ የመንግሥት የአስተዳደር ተቋማት ሙሉ በሙሉ በሸኔ የወደሙ ሲሆን የሚሊሻ ቤቶች፣ ሆቴሎች እና አንዳንድ የከተማው ነዋሪ ቤቶችም የአሸባሪው ጥቃት ሰለባ ሆነዋል ብለዋል።

ቡድኑ በጮቢ ወረዳ ብቻ ከ178 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የመንግስትና የግለሰቦችን ንብረት ማውደሙንም አክለዋል።

አሸባሪው ሸኔ ወደ ከተማዋ በድንገት ዘልቆ ከገባ በኋላ በቆበት የአንድ ቀን ውሎ የሕዝብ አገልግሎት ሰጭ የመንግሥት ተቋማትን ሙሉ በሙሉ ወድሟል።

ሆኖም አሸባሪውን ከወረዳው ለማስወጣት የአካባቢው የፀጥታ ኃይል የተሳካ ኦፕሬሽን በማድረግና 35 የሽብር ቡድኑ አባላትን በመደምሰስ ወረዳዋን ማስለቀቅ ተችሏል ተብሏል።

በወረዳው የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እና የጥቃቱ ሰለባዎችን መልሶ ለማቋቋም ስለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ለመጠየቅ ዋልታ የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎችን በስልክም ሆነ በአካል ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም። ዋልታ ተጨማሪ መረጃ እንዳገኘ ጉዳዩን ይመለስበታል።

በደረሰ አማረ (ከምዕራብ ሸዋ)