የአቃቂ ተገጣጣሚ ቤቶች ፕሮጀክት ምዕራፍ አንድ ሥራ ተጀመረ

የአቃቂ ተገጣጣሚ ቤቶች ፕሮጀክት

ጥር 4/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት ችግርን ለማቃለል በሚል የአቃቂ ተገጣጣሚ ቤቶች ፕሮጀክት ምዕራፍ አንድን ሥራ አስጀመረ።

በፕሮጀክቱ 5 ሺሕ ተገጣጣሚ ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ መያዙም ነው የተገለጸው።

የአቃቂ ተገጣጣሚ ቤቶች በ1 ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቁ ሲሆን ግንባታው የሚካሄድበት ቦታ ከዚህ ቀደም በሕገ ወጥ መንገድ ተይዞ የነበረና አሁን ላይ ነፃ የተደረገ መሆኑን ፕሮጀክቱን ያስጀመሩት የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አበቤ ገልፀዋል።

በከተማዋ ከዓመታት በፊት ለዝቅተኛ ባለገቢ ነዋሪዎች የሚሆኑ መሰል የተገጣጣሚ ቤቶች ግንባታን ለማካሄድ እቅድ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል።

አዲስ አበባ ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት እጥረት ያለባት ከተማ ስትሆን በ2005 በተደረገው የጋራ መኖሪያ ቤት (ኮንዶሚኒየም) ፈላጊዎች ምዝገባ ብቻ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተመዘገቡ ሲሆን ከ900 ሺሕ በላዮቹ ደግሞ እስካሁን ቤቶቹን አላገኙም።

በተስፋዬ አባተ