አብን የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን በባሕርዳር ማካሄድ ጀመረ

አብን የማዕከላዊ ኮሚቴ

መጋቢት 9/2014 (ዋልታ) የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ማዕከላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።

የአብን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጣሂር መሐመድ ስብሰባውን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ያለፉት ጊዜያት የፓርቲው እንቅስቃሴዎች እንደሚዳሰሱና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ አስታውቀዋል።

የማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባም በወቅታዊው የፖለቲካ ሁኔታ አብን ለሕዝቡ ሊያበረክት ስለሚችለው አስተዋጽኦ፣ በቅርቡ በሚደረገው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔ ቅድመ ዝግጅት ላይ፣ ስድስተኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ምን ይመስል እንደነበር እና በሂደቱ የአብን ሚና ምን ይመስል እንደነበር በስፋት ተነስቶ ጥልቅ ውይይት ይደረግበታል ብለዋል።

በስብሰባው በአገሪቱ የተፈጠረውን ጦርነት በመቀልበስ ሂደቱ የአብን ድርሻ እንዴት እንደነበር በስፋት ይፈተሻል ያሉት ኃላፊው የኅልውና ዘመቻው የተመራበት አገራዊ ሁኔታን በመገምገም ቀጣይ ሊከናወኑ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይም ይመክራል ብለዋል።

ሁሉን ዐቀፍ እና አካታች አገራዊ መግባባትን በተመለከተ አብን በተለይ የአማራ ሕዝብን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችልባቸውን ጉዳዮችም ይዳስሳልም ነው ያሉት።

ማዕከላዊ ኮሚቴው የድርጅቱን የቀጣይ አምስት ዓመታት ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎች ላይ ተወያይቶ እንደሚያጸድቅም ይጠበቃል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ስብሰባ አገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ በስፋት የሚተነተን ሲሆን የድርጅቱን የአሠራር ሥርዓቶች በመከተል በኩል መስተካከል ያሉባቸውን ክፍተቶች በሚመለከትም እንደሚመክር አሚኮ ዘግቧል ።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW