አትሌት ዘርፌ ወንድማገኝ ለአምስት ዓመታት ከአትሌቲክስ ውድድር ታገደች

አትሌት ዘርፌ ወንድማገኝ

ሚያዝያ 14/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ዘርፌ ወንድማገኝ የተከለከለ አበረታች መድኃኒት በመጠቀሟ ለአምስት ዓመታት ከአትሌቲክስ ውድድር ታገደች፡፡

አትሌቲክስ ኢንቴግሪቲ ዩኒት ይፋ ባደረገው መረጃ የ21 ዓመቷ የመካከለኛ ርቀት አትሌት ሁለት የተከለከሉ ንጥረ-ነገሮች መውሰዷን አምናለች ብሏል።

አትሌቷ ሦስት ጊዜ ምርመራ የተደረገላት ሲሆን በሁለቱ የተከለከለ አበረታች መድኃኒት መጠቀሟ ተረጋግጧል፡፡

የዓለም አትሌቲክስ አካል የሆነው አትሌቲክስ ኢንቴግሪቲ ዩኒት ባወጣው መግለጫ አትሌቷ ቴስቶስቴሮን የተባለውን እና ኢፒኦ የተሰኘውን አትሌቶች በደማቸው ውስጥ የበለጠ ኃይል እንዲያገኙ የሚያደርገውን ንጥረ ነገር መውሰዷን አምናለች ብሏል፡፡

ዋዳ የተሰኘው ዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች መድኃኒት ተቋም በ2023 ባወጣው ዝርዝር መሠረት አትሌቷ የወሰደችው ንጥረ-ነገር ሕግን የሚጥስ መሆኑ ተዘግቧል።

ከባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ጀምሮ እገዳ ተጥሎባት ምርመራ ላይ የቆየች ሲሆን ዛሬ በይፋ መቀጣቷን አትሌቲክስ ኢንቴግሪቲ ዩኒት አስታውቋል፡፡

አትሌቷ ውሳኔውን በመቃወም ይግባኝ መጠየቅ እንደምትችልም በመግለጫው ላይ ተጠቁሟል፡፡

በሐብታሙ ገደቤ