እስከ 20ሺሕ ብር የሚሸጡ የሐረሪዎች የእጅ ሥራ

መጠናቸው አነስተኛ፣ ያጌጡ፣ ለዓይን የሚማርኩ እና አሰራራቸው በራሱ ብዙ ትርጉም ያለው የአለላ ስፌት ውጤቶች ከ5ሺሕ ብር እስከ 20ሺሕ ብር ድረስ ይሸጣሉ። ይህን የተመለከትነው ለሹዋሊድ ክብረ በዓል በሐረር ከተማ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀ የባህል ዐውደ ርዕይ ላይ ነው።

የአለላ ስፌት ውጤት በሐረሪዎች መንደር ትርጉሙ ብዙ ነው፡፡ ሐረሪዎች በአለላ ስፌት ውጤቶች ያሸበርቃሉ፣ ይዋባሉ፣ ይገለገላሉ፡፡ በሐረሪ የአለላ ስፌት ስራዎች ለተለያዩ አገልግሎት ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ የሐረሪ ሕዝብ እደ ጥበብ ውጤት የሆነው እና በክልሉ በሰፊው የሚመረተው አለላ ስፌት ምርት በዓለም አቀፍ ምድብ የንግድ ምልክት (ብራንድ) ሆኖ መመዝገብ የቻለ ልዩ ጥበብ ነው፡፡

የሐረሪ ክልል መንግስትም ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት ነዋሪዎች በማኅበር ተደራጅተው ታሪካዊ ትስስሩን በጠበቀ መልኩ ባህላዊ የአለላ ስፌቶች እና አልባሳቶችን እንዲያመርቱ ሁኔታዎችን አመቻችቷል፡፡

የሹዋሊድ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ የባህል ዐውደ ርዕይና ፌስቲቫል በሐረር ከተማ ሲከፈት የዕደ ጥበብ ውጤት ሥራዎቿን ለእይታ አቅርባ ያገኘናት የማኅበሩ አባል ሰኣዳ በርከሌ እንደገለጸችልን ሐረሪዎች ለሀዘን፣ ለደስታ፣ ለሰርግ፣ ለጌጥ፣ ለውበት እና ለሁሉም ማኅበራዊ ክዋኔዎቻቸው እነዚህን የእደ ጥበብ ውጤቶች ይጠቀማሉ፡፡ ሐረሪዎች እንደየሁኔታው ለሙሽራ፣ ለአማች እና ለቤተዘመድ የሚሰጥ ታሪካዊ ዳራ ያላቸው ልዩ ልዩ የአለላ ስፌቶችን ያዘጋጃሉ፡፡

በሐረሪዎች መኖሪያ ቤት የገባ ሰው በቀላሉ በግድግዳ ላይ የተሰቀሉ የአለላ ስፌቶችን በመመልከት አንዲት እናት ወንድ ልጅ ወይም ደግሞ ሴት ልጅ መዳሯን በቀላሉ ለማወቅ ይችላል፡፡

በጋብቻ ወቅት ለሙሽሪት የሚሰጡት መዋቢያዎች፣ ጣፋጭ ምግቦች፣ አልባሳት እና መሰል ስጦታዎች በተለያዩ እና ለዚሁ ሲባል በተሰሩ ውብ የአለላ ስፌት ውጤቶች ውስጥ ተደርገው ነው፡፡ ሐረሪዎች ግብር ከፍለው ለሚሰጣቸው የደረሰኝ ወረቀት ማስቀመጫ፣ የሳንቲሞች፣ እጣን እና ሌሎችም ማኖሪያ ሳይቀር ከአለላ ስፌት የሰሩ የእደ ጥበብ አፍቃሪዎች ናቸው፡፡

የዕደ ጥበብ ባለሞያዋ ሰኣዳ በርከሌ ከአዲስ ዲጂታል ዋልታ ጋር በነበራት ቆይታ የአለላ ሰፌት ምርቶቹን ሰርቶ ለመጨረስ ከአንድ ሳምንት እስከ ሶሰት ወራት ጊዜ የሚፈጁ የተለያዩ ሲሆኑ ዋጋቸውም በዚሁ ልክ የሚለያይ ይሆናል፡፡ ለአብነትም ሦስት ወራትን ፈጅቶ በአምስት ቀለማት በደቃቁ ከአለላ፣ አክርማ እና ስንደዶ የተሰራ ለሙሽሮች እቃ ማስቀመጪያነት የሚያገለግል ስፌት እስከ 20ሺሕ ብር እንደምትሸጥ ሰኣዳ ነግራናለች፡፡

ሐረር የሰላም፣ የመቻቻል እና የአብሮነት ከተማነት እውቅና አግኝታ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኒስኮ) የሰላም ተሸላሚ የሆነች መጠሪያዋም የሰላም ከተማ ነው፡፡ የጀጎል ግንብም እንዲሁ የዓለም የቅርስ ስፍራ ሆኖ ኢትዮጵያን ያስጠራ የከተማዋ ፈርጥ ነው፡፡ የሹዋሊድ ባህላዊ ፌስቲቫል በዓለም ቅርስነት በያዝነው ዓመት ለመመዝገብ የበቃ ሲሆን ሌላኛው የሐረሪዎች የደስታና የኩራት ምንጭ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ሐረርን የቱሪስቶች መዳረሻ አድርገዋታል፡፡