አትሌት ግርማዊት ገብረእግዚአብሔር የራስ አል ካማህ ግማሽ ማራቶን ውድድርን አሸነፈች

የካቲት 12/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ግርማዊት ገብረእግዚአብሔር በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በተካሄደው የራስ አል ካማህ የግማሽ ማራቶን ውድድር አሸነፈች።

ዛሬ ማለዳ በተካሄደው ውድድር አትሌት ግርማዊት 1 ሰዓት ከ4 ደቂቃ ከ14 ሴኮንድ ኬንያዊቷን አትሌት ሄለን ኦቢሪን አስከትላ በመግባት አሸናፊ ሆናለች።

የኢትዮ ኤሌክትሪክ ክለብ አትሌት የሆነችው ግርማዊት ጥር 15 ቀን 2014 በተካሄደው 21ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር የሴቶች ውድድር ሁለተኛ መውጣቷን ኢቢሲ አስታውሷል።

ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ቦሰና ሙላቴ 5ኛ ወጥታለች።

በወንዶች ውድድር ደግሞ ዩጋንዳዊው አትሌት ጃኮብ ኪፕሊሞ 57 ደቂቃ ከ56 ሴኮንድ አሸናፊ ሲሆን፤ ኬንያዊው አትሌት ሮጀርስ ክዌሞይ 58 ደቂቃ ከ30 ሴኮንድ በመግባት 2ኛ ደረጃን ይዟል።

ሌላኛው ኬንያዊ አትሌት ኬኔት ኪፕሮፕ ሬንጁ 58 ደቂቃ ከ35 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።

በወንዶቹ ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ሰይፉ ቱራና አምደወርቅ ዋለልኝ በቅደም ተከትል 4ኛና 5ኛ ደረጃን ይዘው ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

የራስ አል ካማህ ግማሽ ማራቶን ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ መካሄዱን ኢዜአ ዘግቧል።