የገንዘብ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከአውሮፓ ኅብረት የምስራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑክ ጋር ተወያዩ

የካቲት 12/2014 (ዋልታ) የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከአፍሪካ ከአውሮፓ ኅብረት የምስራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑክ አኒታ ዌበር (ዶ/ር) ጋር ተወያዩ።

በአፍሪካ ኅብረት እና የአውሮፓ ኅብረት የጋራ ጉባኤ ለመሳተፍ በቤልጂየም ብራስልስ የተገኙት ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናቱ ከጉባኤው ጎን ለጎን ነው ውይይቱን ያደረጉት።

በኢትዮጵያ ሁሉን ዐቀፍ ውይይት በማካሄድ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ተነስተው ውይይት መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ጠቁሟል።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የሰብኣዊ እርዳታ አቅርቦት በተለይም የመድኃኒት አቅርቦትን ተደራሽ ለማደረግ የተከናወኑ ተግባራትን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይም ተወያይተዋል።

መንግሥት በወሰዳቸው አዎንታዊ እርምጃዎች በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ያለውን ፍላጎት ማሳየቱን የገለፁት ሚኒስትሮቹ የትሕነግ የሽብር ቡድን የሚያደረገውን ግጭት ቀስቃሽ እንቅስቃሴን ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ በዝምታ ከመመልከት ወጥቶ ተጠያቂ ሊያደረገው እንደሚገባም ገልጸዋል።