አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የአትሌቲክስ ዊክሊ መጽሔት ምርጥ ሴት አትሌት ተብላ ተመረጠች

አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የአትሌቲክስ ዊክሊ መጽሔት ምርጥ ሴት አትሌት (The Greatest) ተብላ ተመርጣለች።

በአትሌቲክስ ላይ አተኩሮ የሚዘግበው የእንግሊዙ አትሌቲክስ ዊክሊ መጽሔት፣ ባለፉት 75 ዓመታት ውስጥ ምርጥ አትሌትን እንዲመርጡ ለአንባቢዎቹ ጥሪ አቅርቧል።

በዚሁ መሠረት ድምፃቸውን ከሰጡ አንባቢዎች መካከል 31.1% የሚሆኑት የኛ ምርጥ ሴት አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ናት ሲሉ መርጠዋል።

በወንዶቹ ደግሞ ጃማይካዊው የአጭር ርቀት ሯጭ ዩሲዬን ቦልት 55.3% በማግኘት የምርጦች ምርጥ አትሌት ተብሎ ተመርጧል።

አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ በ17.1% ድምፅ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

እንደ አትሌቲክስ ዊክሊ መጽሔት፣ ምርጥ አትሌትን ለመምረጥ የተቀመጡ መስፈርቶች አትሌቶቹ ያገኟቸው ሜዳሊያዎች፣ ያስመዘገቡት ክብረ-ወሰን እና የከወኗቸው የማይረሱ አስደናቂ ክስተቶች ናቸው።

አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በረጅም ርቀት ሩጫ ያሳለፈቻቸው ጊዜያት አስደናቂ እንደነበር መጽሔቱ አውስቷል።