ፌስቡክ ለስደተኞች ሥራ ሰጥቷል ስትል አሜሪካ ከሰሰች

የአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር ፌስቡክ ለስደተኞች ቅድሚያ በመስጠት አሜሪካውያንን በድሏል ሲል ከሷል።

ክሱ እንደሚያመለክተው ማሕበራዊ ድር አምባው 2 ሺህ 600 የሚሆኑ ክፍት የሥራ መደቦች ላይ አሜሪካውያንን መቅጠር ሲገባው አልቀጠረም።

በምትኩ ጊዜያዊ ቪዛ ላላቸው የውጭ ሃገራት ዜጎች ሥራው ተሰጥቷል ሲል የክስ መዝገቡ አስነብቧል።

ፌስቡክ የቀረበበትን ክስ ቢያጣጥልም ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየሠራ እንደሆነ ግን ተናግሯል።

ፌስቡክና ሌሎች ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ኤች-1ቢ የተሰኘውን ቪዛ በመጠቀም ከሌሎች ሃገራት ምጡቅ አእምሮ ያላቸውን ሰዎች ያስመጣሉ።

ሐሙስ ዕለት ፍትህ ሚኒስቴር ያቀረበው ክስ ፌስቡክ ሆን ብሎ የሥራ ቅጥር ሲያወጣ ኤች-1ቢ ቪዛ ላላቸው ሰዎች እንዲሆን አድርጎ ነው ይላል።

ሚኒስቴሩ ለሁለት ዓመት ምርመራ ካደረግኩ በኋላ ነው ክሱን የመሠረትኩት ያለ ሲሆን፣ ክሱ ተሰሚነት የሚያገኝ ከሆነ ፌስቡክ “ሥራ ለነፈጋቸው አሜሪካዊያን” መክፈል የነበረበትን ያክል ገንዘብ ሊቀጣ ይችላል።

የሚኒስቴሩ ሠራተኞች የሆኑት ጠበቃ ኤሪክ ድራይባንድ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መሰል ሕገ ወጥ የሆነ ተግባር ከመከወን እንዲቆጠቡ ማሳሰባቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።