አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ ከአለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ጋር ተወያዩ

መጋቢት 28/2013 (ዋልታ) – የሶማሌ ክልል ምክትል ርእስ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ ከአለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ስቴቨን ዌሬ ኦማሞ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ አቶ ሙስጠፌን ጨምሮ በክልሉ የሚመለከታቸው ቢሮ ኃላፊዎች በተገኙበት የተካሄደ ሲሆን፣ በክልሉ በተፈጠረው የዝናብ አጥረት ምክንያት ለተከሰተው ድርቅ እየተሰጠ የሚገኘውን ምላሽ አስመልክቶ ማብራርያ ተሰጥቷል።
የክልሉ መንግስት በክልሉ የተከሰተውን ድርቅ በቁጥጥር ስር ለማዋልና በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በጀት በመመደብ ለድርቅ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የውሃና የእንስሳት መኖ እያቀረበ እንደሚገኙ ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።
ክልሉ ድርቅ በተከሰተባቸው አከባቢዎች በራሱ አቅም ምላሽ እየሰጠ ቢሆንም የምግብና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት አቶ ሙስጠፌ፣ በዚህ ላይ የለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
በክልሉ ለውጡን ተከትሎ ህዝቡን የሰላምና የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የተሰሩ ውጤታማ ስራዎች በአሁኑ ጊዜ በተከሰተው ድርቅ ዝቅ እንዳይሉ ለጋሽ ድርጅቶች የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
የአለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጲያ ተወካይ ዶ/ር ስቴቨን በበኩላቸው፣ በሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ በቀጣይ ለክልሉ ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸው፣ በክልሉ የተከሰተው ድርቅ እያስከተለ የሚገኘው ችግር መገንዘባቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ በክልሉ ያለውን ችግር ለሎችም አጋር ድርጅቶች በማስረዳትና ሀብት በማሰባሰብ በክልሉ ለተከሰተው ድርቅ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድና የክልሉ መንግስት በሳል አመራር የጅግጅጋ ከተማን ጨምሮ በክልሉ የተለያዩ አከባቢዎች የሚታየውን ሁለተናዊ ለውጥን ማድነቃቸውን ከክልሉ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።