ነሃሴ 9/2013(ዋልታ) – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በወሎ ግንባር በአምባሰል ወረዳ ውጫሌ ከተማ የሚገኘውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባላት በአካል ተገኝተው አበረታትተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት የሀገር መከላከያ ሰራዊት አገሪቷ የገጠሟትን ፈተናዎች ፊት ለፊት በመፋለም ከፍተኛ መስዋዕትነትን እየከፈለ ያለ ህዝባዊ ሰራዊት መሆኑን ገልጸዋል።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን አገርን ለመበተን ባለው ፍላጎት ሠራዊቱን ከጀርባ ለመውጋት ቢሞክርም በጀግናው የሠራዊቱ አባላትና መላው ኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ እየደረሰበት እንደሆነ አስታውቀዋል።
በአማራና አፋር ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች አሸባሪው ቡድን ህዝቡን ከመኖሪያ ቀየው በማፈናቀል፣ በመረሸንና ሀብትና ንብረቱ እንዲወድም በማድረግ፣ ህጻናትና ሴቶችን በመድፈር፣ የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል የተዘረጉ መሰረተ ልማቶችን በማውደምና ሌሎች ያደገበትን ሴራዎች ሁሉ ህዝብ ላይ በመፈጸም ኢትዮጵያ ጠልነቱን በተግባር እያሳየ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያ ኩራትና የክብር ማሳያ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ደመቀ መከላከያ ሰራዊቱ፣ ሌሎች የጸጥታ ኃይሎችና በመላ ኢትዮጵያዊያን ትግል ይህ አሸባሪ ቡድን ተደምስሶ ኢትዮጵያ አሸናፊ የምትሆንበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ተናግረዋል።
በቀጣይም ህዝቡ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ሊፈጽሙት የሚችሉትን ማንኛውንም ጥቃት የሚመጥን የስነ ልቦናና ወታደራዊ ዝግጁነቶችን በመላበስ በህልውናው ላይ የመጣን ጠላት ለመደምሰስ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንዲያግዝ ጥሪ ማቅረባቸውን ከደቡብ ወሎ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።