አቶ ደመቀ መኮንን ከአፍሪካ ሕብረት ኮምሽን ምክትል ሊቀ-መንበር ጋር ተወያዩ

የአፍሪካ ሕብረት ኮምሽን ምክትል ሊቀ-መንበር ዶ/ር ሞኒክ ንሳንዛባጋንዋሚያዝያ 01/2013 (ዋልታ) – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በቅርቡ የአፍሪካ ሕብረት ኮምሽን ምክትል ሊቀ-መንበር ሆነው የተመረጡት ዶ/ር ሞኒክ ንሳንዛባጋንዋን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

አቶ ደመቀ የአፍሪካ ሕብረት ኮምሽኑ ምክትል ሊ/መንበር ሆነው በመመረጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፣ በቀጣይ በሚኖራቸው የስራ እንቅስቃሴ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አረጋግጠዋል ።
በመቀጠልም አቶ ደመቀ በቅርቡ በኪንሻሳ የተካሄደው የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ድርድርን በተመለከተ ያብራሩላቸው ሲሆን ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ማግኘት እንዳለባቸው በማመን በአፍሪካ ሕብረት አስተባበሪነት የሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር እንዲቀጥል በኢትዮጵያ በኩል ጽኑ እምነት ያለ መሆኑን ገልፀዋል።
በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በመሻሻል ላይ መሆኑን ለምክትል ሊ/መንበሯ አብራርተዋል።
ዶ/ር ሞኒክ ንሳንዛባጋንዋን በበኩላቸው ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መርህ በአፍሪካ ሕብረት በኩል በጽኑ የሚታመን መርህ መሆኑን ገልጸው፣ ኢትዮጵያ በዚህ አንጻር ለያዘችው አቋም ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት ያጋጠመውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የሕብረቱ ሰራተኞች ክትባት አንዲደርሳቸው በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ድጋፍ አንዲደረግ ጥያቄ አቅርበዋል።
አቶ ደመቀ ለአፍሪካ ሕብረት ሰራተኞች ተገቢው የክትባት አገልግሎት እንዲደርሳቸው ማድረጉ ተገቢ መሆኑን ገልጸው፣ ለተፈጻሚነቱም ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገልፀዋል።
በመጨረሻም አቶ ደመቀ መኮንን ለዶ/ር ሞኒክ ንሳንዛባጋንዋን መልካም የስራ ዘመን አንዲሆንላቸው ተመኝተው፣ ለስራቸው ስኬትም በኢትዮጵያ በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አረጋግጠዋል።
(ምንጭ፡- የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ )