መጋቢት 30/ 2013 (ዋልታ) – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከዴንማርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄፕ ኮፎድ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በትግራይ ክልል ያለውን የሰብአዊ ድጋፍ በተመለከተ ገለጻ ያደረጉት አቶ ደመቀ በመጀመሪያ ዙር ለ4 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች ድጋፍ መደረጉንና ሁለተኛ ዙር ድጋፍ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡
ሚኒስትሩ ከሰብአዊ ድጋፉ ውስጥ 70 በመቶው በመንግስት መሸፈኑን ጠቅሰው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንዲጨምር ጠይቀዋል፡፡
በክልሉ ካሉ ጥቂት ቦታዎች በስተቀር አብዘኛው ቦታዎች ተደራሽ መሆናቸውን፣ የሰብአዊ ድጋፍ ለሚያደርጉ አካላት ያለገደብ እንዲቀሳቀሱ ሁኔታ መመቻቸቱን ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና በተመድ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የጋራ ምርመራ ለመጀመር ዝግጅት ማድረጋቸውን እንዲሁም የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አክለውም የኤርትራ ወታደሮች እንዲወጡ ከኤርትራ መንግስት ጋር ውይይት መደረጉን፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በተጨማሪም የአፋር ክልል ልዩ ኃይል በክልሉ የህግ በላይነት ለማስከበር በየአካባቢዎቻቸው እንዲሰማሩ በፌዴራል መንግስት የታዘዙ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪ ስድስተኛውን ሃገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ እንዲከናወን ጠንካራ ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ መኖሩን ፣ ምርጫውን እንዲታዘቡ የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ለበርካታ አካላት ግብዣ መላኩን አውስተዋል፡፡
ከኢትዮ-ሱዳን ድንበር ውዝግብ ጋር ተያይዞ በሁለቱ ሃገራት መካከል ያሉ ልዩነቶችን ለመፍታት የተቀመጡ አሰራሮች በሱዳን በኩል መጣሳቸውንና ሱዳን የዓለም አቀፍ ህግ መጣሷን አስረድተዋል፡፡
የድንበር ውዝግቡ በውይይት ለመፍታት ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን በመጥቀስም ሱዳን ከሉዓላዊ የኢትዮጵያ ግዛት ለቃ እንድትወጣና ለውይይት ዝግጁ እንድትሆን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
የዴንማርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄፕ ኮፎድ በበኩላቸው ስለተደረገላቸው ማብራሪያ አመስግነው፤ መንግስታቸው በትግራይ ክልል እየተደረገ ያለውን የሰብአዊ ዕርዳታ ለመደገፍ እንዲሁም በሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ እና በስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ ዙሪያ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡