አካል ጉዳተኛነት ከምንም ነገር አያገልም- ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ

ጥር 12/2014 (ዋልታ) የብሔራዊ ዊልቼር ቅርጫት ኳስ ቡድን አባላትን ለመሸኘትና የመልካም እድል ምኞታቸውን ለመግለጽ የተገኙት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አካል ጉዳተኛነት ከምንም ነገር አያገልም ሲሉ ተናገሩ።

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በምታስተናግደው 11ኛው የአፍሪካ ዊልቼር ቅርጫት ኳስ ውድድር ላይ ብሔራዊ ቡድኗ በሁለቱም ፆታ ለማሳተፍ በዝግጅት ላይ ትገኛለች።

በወንዶች 6 በሴቶች 4 ሀገራት የሚሳተፉበት ይህ ውድድር በዱባይ ለሚዘጋጀው 14ኛው የዓለም ዊልቼር ቅርጫት ኳስ ውድድር አፍሪካን የሚወክሉ ሀገራት የሚለይበት መድረክ ነው።

ዛሬ በአራት ኪሎ ወጣቶች እና ስፖርት ማእከል በሁለቱም ፆታ ለውድድሩ ዝግጅት ሲያደርጉ የነበሩትን የቡድኑ ተጫዋቾች ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ በተገኙበት አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል።

ፕሬዝዳንቷ ለውድድሩ ወደ ኢትዮጵያ ከሚመጡት 5ቱ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ጥሩ ወንድማዊ ትስስር እንዲፈጥሩና በእንችላለን መንፈስ ውድድሩን ለማሸነፍ እንዲነሱ ተጫዋቾቹን አበረታተዋል።

በመድረኩ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ እና የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት የተገኙ ሲሆን የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ከፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ እና ከሚኒስትሩ ቀጄላ እጅ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በቡድን አንበሎቻቸው አማካኝነት ተረክቧል። ጥሩ ውጤት በማምጣት ዱባይ በምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ላይ እንዲሳተፉም አደራ ተጥሎባቸዋል።

ውድድሩ የፊታችን እሁድ ጥር 15 ሲጀምር በወንዶች አዘጋጇ ኢትዮጵያን ጨምሮ አልጀሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ግብፅ እና ዴሞክራቲክ ኮንጎ በሴቶች ኢትዮጵያ፣ አልጀሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኬንያ እንደሚሳተፉ ኤኤምኤን ዘግቧል።