ኢንግሊዝ የኢትዮጵያ መንግሥት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እያደረገ ያለውን ጥረት አደነቀች

ጥር 13/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ መንግሥት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እያደረገ ያለውን ጥረት የእንግሊዝ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ አደነቁ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከእንግሊዝ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ እና በሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ ሚኒስትሯ ቪኪ ፎርድ ሀገራቸው የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ወዳጅ መሆኗን ገልጸው እንግሊዝ ከኢትዮጵያ ጋር ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ እየሰራች መሆኗን አንስተዋል።

ሚኒስትሯ መንግሥት ሰላም እንዲሰፍን በሚያደረገው ጥረት ወደ ትግራይ ክልል መከላከያ ሠራዊት አሰማርቶ ዘመቻ ላለማድረግ ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉን አሳታፊ ብሔራዊ ውይይት እንዲደረግ እና በቅርቡ እስረኞችን መፍታቱ የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን አንስተዋል።

ሚኒስትሯ ችግር በተፈጠረባቸው አካባቢዎች በአስገድዶ መድፈር ወንጀል የተሳተፉ አካላት አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎ ለጥፋታቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን ከተባበሩት መንግሥታት አቻው ጋር ስላደረገው ምርመራም አንስተው ተወያይተዋል።

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው መንግሥት ሰብኣዊ ርዳታ እንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎል እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አብራርተዋል።

መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት እርዳታ የጫኑ አውሮፕላኖች ወደ መቐሌ በየዕለቱ በረራ እንዲያደርጉ ፍቃደኛ ነው ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከአሁን በፊት ለሰላም የተዘረጉ በርካታ አማራጮች ማምከኑንም አብራርተዋል።

የሽብር ቡድኑ የቀውሱ ጠንሳሽ መሆኑን እና በኋላ ላይም መንግሥት ለሰብኣዊ እርዳታ ሲል ያሳለፈውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ወደ ጎን በማድረግ ቀውሱን ወደ ሌሎች ክልል እንዲስፋፋ አድርጓል ነው ያሉት።

የሽብር ቡድኑ አሁንም የሰብኣዊ እርዳታ ሂደቱን ለመረበሽ በአፋር አብአላ በኩል የጥቃት እየፈፀመ መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የተመደበውን ነዳጅ ለሌላ ተግባር እያዋለ እና የአሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ እየረበሸ ነው ብለዋል።

አምባሳደር ሬድዋን በንፁኃን ላይ የሰው አልባ የአውሮፕላን ጥቃት እየተፈፀመ ነው የሚለው መረጃ መሰረተ ቢስ ውንጀላ ነው ያሉ ሲሆን የሽብር ቡድኑ አሁንም በአጎራባች ክልሎች ጥቃት መፈጸሙን አላቆመም ነው ያሉት።

አምባሳደር ሬድዋን ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ የእርዳታ ተደራሽነቱን አንድ አካባቢ ብቻ ማተኮሩን ትቶ ጉዳት ወደ ደረሰባቸው ሁሉም አካባቢዎች እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ የሕወሓት የሽብር ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች የፈፀመውን የሽብር ጥቃት ሊያወግዝ ይገባልም ነው ያሉት።

እንግሊዝ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ያሳየችውን ፍላጎት አድንቀው የኢትዮጵያ ወሳኝ የልማት አጋር መሆኗንም ለሚኒስትሯ ማንሳታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡