አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ ሥልጣን ተረከቡ

ግንቦት 16/2014 (ዋልታ) ተመራጩ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ ከቀድሞው የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሙሐመድ አብዱላሂ (ፋርማጆ) ሥልጣን ተረክበዋል።

ከቀናት በፊት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያካሄደችው ሶማሊያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ እና ምክትል አፈጉባኤ፣ ሚኒስትሮች፣ የመንግሥት ሠራተኞች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የሥልጣን ርክክብ ሥነ-ሥርዓት ተደርጓል።

ዘጠነኛው የሀገሪቱ መሪ የነበሩት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ (ፋርማጆ) ለተመራጩ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ ሥልጣናቸውን ማስረከባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ ከምርጫ በኋላ ባስተላለፉት መልክት ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በሁለቱ አገሮች የጋራ ጉዳይ ላይ በትብብር እንደሚሰሩ መናገራቸው የሚታወስ ነው።