ግንቦት 07/2013 (ዋልታ) – አዲስ አበባን የኢትዮጵያ የባህል ማዕከል እናደርጋታለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ የፊቼ-ጨምበላላ በዓል በአዲስ አበባ ከተማ አዘጋጅነት በዛሬው ዕለት ተከብሯል፡፡
ምክትል ከንቲባዋ ፊቼ ጨማባላላ የሲዳማ ብሄር ዘመን መለወጫ ይሁን እንጅ በውስጡ የመልካም አስተዳደር፣ የሰው ልጆች እኩልነት፣ አብሮነት፣ ሰላም፣ ፍቅር እና መከባበር የመሳሰሉ ለተፈጥሮ አስፈላጊ የሆኑ ትሩፋቶችን የያዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ስለሆነም ባህሉ እንደ በዓል ብቻ ለእለት ተከብሮ የምታለፍ ብቻ ሳይሆን ከሲዳማ ህዝብ ለኢትዮጵያዊያን ብሎም ለዓለም ህዝብ የተበረከተ ውድ ባህል በመሆኑ ከነሙሉ ክብሩ እና እሴቶቹ ሳይበረዝ ለትውልድ እንዲተላለፍ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
ምክትል ከንቲባዋ በኢትዮጵያ ያሉ በርካታ የብሔር ብሄረሰቦችን ቱባ ባህሎችን መጠበቅ ለቱሪዝም ዘርፍ ማዋል እንደሚገባ የገለጹት ምክትል ከንቲባዋ፣ አዲስ አበባን የኢትዮጵያ የባህል ማዕከል ለማድረግ በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከባህል ማዕከል መገንቢያ ቦታ ከመስጠት በተጨማሪ የፊቼ-ጨምበላላ በዓል በከተማዋ እንዲከበር ላደረገው ድጋፍ በከልሉ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
ባህሉ ለትውልድ እንድተላለፍ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን እና መንግስት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው በመርሐግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ፊቼ ጨምባላላ ባሕላዊ ይዘቱንና ታሪካዊ ሁነቱን በጠበቀ መልኩ ለትውልድ እንዲተላለፍ የመስኩ ምሁራን እና የሚመለከታቸው አካላት የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በሚያሳድግ መልኩ በትብብር ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
“ፊቼ-ጨምበላላ ” የሰላም፣ የመከባበር፣ የፍቅር፣ የአብሮነት፣ የመቻቻል እና የእርቅ ተምሳሌት በሚል መሪ ቃል በከተማ አስተዳደሩ የተከበረ ሲሆን፣ በበዓሉ የተለያዩ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሲዳማ ክልል ተወላጆች ተገኝተዋል።
የፍቼ ጫንባላላ እንደፈረንጆቹ የዘመን ቀመር በ2015 በዓለም የሳይንስ፣ ትምህርት እና ቅርስ ጥበቃ (ዩኒስኮ) የኢትዮጵያ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ ይታወሳል፡፡
(በሚልኪያስ አዱኛ)