አዲስ አበባ እና የቻይናዋ ፉጃን ክፍለሀገር ስምምነት

አዲስ አበባ ከተማ ከቻይናዋ የፉጃን ክፍለሀገር ጋር የእህትማማች ከተሞችን ለመመስረት የሚያስችል የፊርማ ስነ-ስርዓት ዛሬ በቤጂንግ ከተማ ተካሄዷል፡፡

በዚህ የፊርማ ስነ-ስርዓት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን በመወከል በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በቦታው ተገኝተው በሰነዱ ላይ ፈርመዋል፡፡

ሰነዱ በአዲስ አበባ እና በፉጃን ክፍለሀገር መካከል በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በግብርና፣ በባህል፣ ቱሪዝም፣ ትምህርት፣ ስፖርት እና በጤና መስክ ዙሪያ ላይ ልምድ ልውውጥና ትብብር ማድረግ እንደሚያስችል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በፌስ ቡክ ገጻቸው አስታውቀዋል።

ይህ ስምምነት በኢትዮጵያ እና በቻይና ህዝቦችና መንግስታት መካከል ያለውን ትስስር የበለጠ እንደሚያጠናክር እምነቴ የፀና ነውም ብለዋል፡፡

የቻይና መንግስት በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ሁለገብ የልማት እንቅስቃሴ በመደገፍ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ከኢትዮጵያ ጎን በመሰለፍ የኢትዮጵያ የምንጊዜም አጋር መሆኑን በተግባር ያስመሰከረ መንግስት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡