አዲስ ዋልታ የኢትዮጵያ ሚዲያ ካፕ ሻምፒዮን ሆነ

የካቲት 17/2016 (አዲስ ዋልታ) በ13ኛው ቢጂአይ ኢትዮጵያ ሚዲያ ካፕ አዲስ ዋልታ ቴሌቪዥን ሪፖርተር ጋዜጣን 3ለ2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ዋንጫውን አነሳ።

ለአዲስ ዋልታ ሦስቱንም ግቦች ሙሉብርሃን አበበ አስቆጥሯል።

አዲስ ዋልታ ካደረጋቸው ሦስት የምድብ ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎና በአንዱ አቻ ተለያይቶ በግብ ክፍያ ተበልጦ ከምድቡ ሁለተኛ ሆኖ ነው ወደ ጥሎ ማለፍ የተቀላቀለው።

አዲስ ዋልታ በጥሎ ማለፍ አትዮ ዲጄን፣ በሩብ ፍጻሜ ሆፕ ቻናልን፣ በግማሽ ፍፃሜ ደግሞ አርትስ ቴሌቪዥንን በማሸነፍ ነው ለፍጻሜ የደረሰው፡፡

አዲስ ዋልታ በነበረው 11 ጊዜ የውድድሩ ተሳትፎ ለፍጻሜ ሲደርስ ይህ የመጀመሪያው ሲሆን ባለፈው ዓመት ውድድሩን በ4ኛነት ማጠናቀቁ ይታወሳል።

22 ማዞሪያ መክሊት ህንፃ አካባቢ በሚገኘው የፉትሳል ሜዳ በተካሄደው ውድድር አርትስ ቴሌቪዥን ከብስራት ኤፍ.ኤም ጋር ለደረጃ የተጫወቱ ሲሆን ብስራት ኤፍኤም አርትስ ቴሌቪዥንን 6ለ2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ውድድሩን በሦስተኛነት ማጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

በውድድሩ የ13 ዓመታት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 32 ሚዲያዎች በተካተቱበት ውድድር ከ450 በላይ የሚዲያ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል።