አገራት ኢትዮጵያ ካጋጠማት ፈተና ለመጠቀም ጥረት እያደረጉ ነው

ነሃሴ 9/2013(ዋልታ) – ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ወቅታዊ ፈተና በመጠቀም በርካታ ቡድኖችና ሃገራት አላማቸውን ለማሳካት የተቀናጀ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ዶረን ኒኮል የተባሉ ጸሃፊና መምህር ገለጹ።

ስለኢትዮጵያ የውስጥ ግጭት እውነቱን ማን ይናገር? በሚለው ጽሁፋቸው አሸባሪው ህወሃት በመከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ክህደት ተከትሎ በትግራይ ክልል በተካሄደው ህግ የማስከበርም ሆነ የህልውና ዘመቻ ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ህጻናት አንገብጋቢ የምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው የተባበሩት መንግስታት የህጻናት እርዳታ ድርጅት ዩኒሴፍ ቢወተውትም ህወሃት ከአርባ አመታት በፊት የሰራውን ድራማ በመድገም በህጻናቱ ህይወት ላይ ቁማር መጫወት መምረጡን ገልጸዋል።

በዚህም 5 ሚሊየን የሚሆኑት የትግራይ ክልል ነዋሪዎች አለም አቀፉ ማህበረሰብ የላከው የእርዳታ ይደርሰናል እያሉ በመጠበቅ ላይ ናቸው ብለዋል ጸሀፊው።

ከቀይባህር ባለው የንግድ መስመር በተጨማሪም አሜሪካ ከአካባቢው ሃገራት ስታጋብሳቸው የነበሩት ዚንክና ፎስፌትን የመሳሰሉ ውድ ማእድናት ምክንያት ከቻይና ጋር ሁለንተናዊ ፍጥጫ ውስጥ ስለምግባቷ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሯን አን ዤራልድን ዋቢ ያደረጉት ጸሃፊው አሜሪካ በህዝብ ከተመረጠው የአብይ አህመድ አስተዳደር ይልቅ ይሄንን ፍላጎቷን ሲያስጠብቅላት የቆየውን ህወሃት መንበሩ ላይ ለመመለስ ድጋፍ እያደረገችለት ነው ብለዋል።

ጸሃፊው አሜሪካ እ.ኤ.አ ከ1976 ጀምሮ በአሻባሪዎች መዝገባ ውስጥ ያስገባችውን ህወሃት በድርጊቶቹ ምክንያት የኢትዮጵያ መንግስትም በዚሁ አመት ግንቦት ላይ አሸባሪ ሲል መሰየሙ ሊያስገርም እንደማይገባና ድርጅቱ ለአሜሪካ መንግስታት ባሳየው ታማኝነት ምክንያት ለሃያ ሰባት አመታት በተከተለው አምባገነናዊ አገዛዝ ዜጎችን ጸጥ አሰኝቶ ከማኖሩም በላይ ያደረሳቸውን ሰቆቃዎችም ሲነገሩ እንደማይሰማ ተናግረዋል።

ከጥቂት ቀናት በፊት ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት ሳማንታ ፓወርን ጨምሮ የአሜሪካ ባለስልጣናት ህወሃት በአማራና አፋር ክልል ወረራ አድርጎ በርካቶች ሲሞቱ ሲፈናቀሉና ንብረት ሲወድም የላሊበላ ቅርሶች ጉዳይ እንደሚያሳባቸው ከመግለጽ ባለፈ ለማውገዝ እንኳን አለመፈለጋቸው ድርጅቱና አሜሪካ ያላቸውን ስር የሰደደ ትስስር ያሳያልሲሉም ገልጸዋል።

ይህን ጉዳይ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ኦባማም ሆነ የቢልክሊንተን አስተዳደሮች የድርጅቱን ክፋቶችና ጥፋቶች በዝምታ ሲያልፉ ነበር ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት አርሶ አደሮች እንዳርስ እና በጣም አስፈላጊ ዕርዳታ ወደ ክልሉ እንዲገባ ለማድረግ የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ቢያደርግም የህወሓት አባላት እና ደጋፊዎች የተሰጠውን የጥሞና ጊዜ በመጠቀም በአፋርና አማራ ክልሎች ወረራ ፈጽሟል።

ከዚህም በተጨማሪ ትግራይ ውስጥ የሚሰሩ 40 ጊዜያዊ አስተዳዳሪዎች ገድለዋል።

በኢትዮጵያ ለውጥ እስኪመጣ  ድረስ በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች በመንግስት መስሪያ ቤቶችም ሆነ በመኖሪያ መንደሮች ውስጥ ዜጎችን አንድ ለአምስት በሚባል የስለላና የቁጥጥር መዋቅር በማያያዝ የአፈና ስርአቱን ማጠናከሩን ያስታወሱት ጸሃፊው በትግራይ ያሉ ዜጎች ጥያቄም ሆነ ተቃውሞ እንዳያነሱ ለማድረግ አደረጃጀቱን የተጠቀመበት በመሆኑ ህብረተሰቡ ከህወሃት ውጪ እንዳያስብ ብሎም ሰብአዊ እርዳታ እንዳይደርሰው እንዳደረገው ገልፀዋል።

በአሜሪካ ባለስልጣናት “ለፍላጎታችን መሟላት ይጠቅመናል” በሚል የሚታገዘው ህወሃት ላለፉት 30 አመታት ከ30 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብና በርካታ ወርቅ ከሃገር አሽሽቶ ኢትዮጵያ ላይ የህልውና ስጋት በመፍጠር ላይ የሚገኝ መሆኑን በመረዳት አፍሪካ ላይ ያላቸውን ፖሊሲ መለስ ብሎ ለመፈተሽ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ አስረድተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።