አፈ-ጉባኤ አደም ፋራህ ለቤልጅየም ጠቅላይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ አደረጉ

ሰኔ 04/2013 (ዋልታ) – የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አደም ፋራህ ለቤልጅየም ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ዲክሮ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል፡፡

አፈ-ጉባኤው አደም ፋራህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መልእክትን ለቤልጅየም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተላልፈዋል፡፡

አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ መጪውን ሀገር አቀፍ ምርጫን አስመልክቶ በወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ፣ እየተካሄደ ያለውን የለውጥ ስራ፣ በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ እና የህዳሴ ግድብ የሚደረጉ የሶስትዮሽ ድርድር ጭምር ገለፃ አድርገዋል፡፡

በተመሳሳይ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ የጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አህመድን መልዕክት ለኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ አድርሰዋል፡፡

ሚኒስትሩ ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት፣ በትግራይ ክልል እየተካሄደ ስለሚገኘው የመልሶ ግንባታና የሰብአዊ ድጋፍ በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ በበኩላቸው፣ በተነሱት የውይይት ሀሳቦች ላይ ለኢትዮጵያ ያላቸውን አጋርነት ገልጸው፣ የናይል ተፋሰስ ሀገራት በጋራ ጉዳዮቻቸው ዙሪያ በሚኒስትሮችና በመሪዎች ደረጃ ጠንካራና ቀጣይነት ያለው ምክክር ሊያካሂዱ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡