ኢትዮጵያና የአለም ባንክ የ200 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ተፈራረሙ

ሚያዚያ 29/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያና የአለም ባንክ የ8.4 ቢሊዮን ብር የብድር ስምምነት ዛሬ በገንዘብ ሚኒስቴር አዳራሽ በተካሄደ ስነስርአት ተፈራረሙ፡፡

የብድር ገንዘቡ በዋነኝነት ኢትዮጵያ በ10 አመቱ መሪ የልማት እቅድ ላለመችው መጠነ ሰፊ የልማት ግብ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ ተግባራዊ ለማድረግ የሚውል ሲሆን ይህም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በቴሌኮሙኒኬሽን መስክ ሰራ በመፍጠርና የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ  የዲጂታል ኢኮኖሚ ስትራቴጂውን እውን የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል፡፡

ይህ የኢትዮጵያ ዲጂታል ፋውንዴሽን ፕሮጀክት የሚል ስያሜ የተሰጠውና በብድር ገንዘቡ ተግባራዊ ሊደረግ የታቀደው ፕሮጀክት ለአምስት አመታት ያህል የሚዘልቅ ሲሆን የፕሮጀክቱ ዋንኛ አላማ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አካታችነት፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዋጋ ተመጣጣኝነትና የዲጂታል ስራ ፈጠራ ናቸው ተበሏል፡፡

በዚህም መሰረት በዲጂታል ቴክኖሎጂ አካታችነት የሀገሪቱ የኢንተርኔት ተደራሽነትና የተጠቃሚዎች  ቁጥርና ስብጥር እንደሚያድግ፣ በዲጂታል ቴክኖሊጂ ዋጋ ተመጣጣኝነት ረገድም ለዲጂታል አገልግሎት የሚከፈለው ወርሀዊ ክፍያ ተመጣጣኝ እንደሚሆን እንዲሁም በዲጂታል የስራ  ፈጠራ ዘርፍ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚፈጠሩ የስራ መስኮች የሚስፋፉበትና ዘላቂነታቸው የሚረጋገጥበት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠርም ታውቋል፡፡

የብድር ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል የገንዘብ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ የፈረሙ ሲሆን በአለም ባንክ በኩል ደግሞ የአለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳንና የኤርትራ ተጠሪ ሚ/ር ኦስማን ዲዮን ፈርመዋል፡፡