ኢትዮጵያውያንን ያስተሳሰረው መግነ ጢሳዊው ኃይል – ዓድዋ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ በዘመናት ታሪኳ ውስጥ በልበ ሙሉና ክንደ ብርቱ ጀግኖቿ ነፃነቷን አስጠብቃ፣ አንድነቷን አስመስክራ፣ እምነቷን አጥብቃ እና ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ አኩሪ ድል ያጎናፀፈችበት ብስራት  ነው አድዋ፡፡ ከአድዋ በፊት በነበሩ ዓመታት በርካታ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ጋዜጦች መላው ጥቁር አፍሪካ በአውሮፓ ሙሉ ቁጥጥር ስር ለመሆን መቃረቡን በእርግጠኝነት ይፅፉ ነበር የአሜሪካው አትላንታ ኮንስቲትዩሽን ጋዜጣ ‹‹መላዉ አፍሪካ በአውሮፓ መንግስት ቅርምት የምትጠናቀቅበት ቀን ቀርቧል›› የሚል ሐሣብ የያዘ ጽሑፍ አስፍሮ ነበር፡፡

አውሮፓውያኑ በአሜሪካ ያሳኩትን የዘር የበላይነት በአፍሪካ ለመድገም ተዘጋጅተዋል በአሜሪካ ቀይ ህንዶችን በማስወገድ ለራሳቸው ዝርያ መኖርያ መፍጠር የቻሉበትን ብቃት በአፍሪካ ለመድገም የጥቁር አፍሪካ ዝርያዎችን በቅርቡ ማጥፋት የጀምራሉ፡፡›› እያሉ በአዉሮፓ የዘር እና የፖለቲካ የበላይነት ስብከቶች ዝተው ነበር፤ ነገር ግን እንዳሰቡት ሳይሆን ቅዠት ሆኖ ቀረ፡፡

የአድዋ ድል የአውሮፓን የዓለም ፖለቲካ እና ዘር ልዕለ ሀይል ከመሆን ለማስቆም በር ከፋች የሆነ ብቸኛው ልዩ አጋጣሚ ነበር የጦርነቱ መንስኤም የዉጫሌ ዉል በሚያዚያ 25 ቀን በ1881 ዓ.ም በኢትዮጵያና በጣልያን መንግስታት መካከል በተፈረመ ዉል ነበር። ዉሉን የፈረሙት በኢትዮጵያ በኩል ግራዝማች ዮሴፍ ንጉሴ ሲሆኑ ጣሊያንን በመወከል ደግም ካዉንት ፔትሮ አንቶሎኒ ነበሩ ይህ ስምምነት የአማርኛና የጣሊያንኛ ትርጉሙ የሚቃረን ከመሆኑ ባሻገር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጋፋ ውል በመሆኑ የዉጫሌ ዉል የአድዋ ጦርነት መንስኤ ሊሆን ቻለ። የጦርነቱ መነሻ ዋናው ምክንያት አንቀፅ 17 ላይ የአማርኛውና የጣልያንኛው ትርጉም የተዛባ በመሆኑ ነበር፡፡

የአማርኛ ትርጉሙ የኢትዮጵያ ነገስታት ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ በጣሊያን መንግስት በኩል መላላክ የቻላቸዋል የሚል ሲሆን የጣሊያንኛ ትርጉሙ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ግንኙነት ከፈለገ በጣሊያን መንግስት በኩል መሆን አለበት የሚል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የኢትዮጵያን ክብር እና የኢትዮጵያን ማንነት የሚጋፋ ዉል ነበር፡፡

ይህንን በተንኮል መርዝ  የተገመደ እና  የተሸረበ ሴራ ነበር  መስማት አይቀርምና ይህ ውል እቴጌ ጣይቱ ጆሮ ደረሰ  የሰሙትን ነገር ማመን አቅቷቸው ቁጣቸው እንደ አራስ ነብር ገንፍሎ ከመቀመጫቸው አስነሳቸው ከዛም ከእልፍኙ አዳራሽ አንዴ ወደ ግራ አንዴ ወደ ቀኝ  በረዥሙ ጫን ጫን እየተነፈሱ በደርባባ ሰውነታቸው እየተንጎራደዱ ጎላ ጎላ ያሉ አይኖቻቸውን ከእልፍኙ በር ትይዩ ከሚታየዉ የጠራ ሰማይ ላይ  አሳረፉት።  እናም በሃሳብ ጭልጥ አሉ ድንገት የሆነ ሀሳብ ስሜታቸውን ቀየረው።  እናም ፈንጠር ብለው ዙፋናቸው ላይ ተቀመጡ ሆኖም የተሻለ ውሳኔ ለመፍጠር ሀሳብ ሲያውጠነጥኑ ሲያወጡና ሢያወርዱ ሰነበቱ።

እቴጌ  አስቀድመው እኒህ ፈረንጆች የሚያወሩት እና በተግባር የሚያውሉት የማይገናኝ በተንኮል የተመረዘ መሆኑን  ከሀሳባቸው ሄድ መለስ እያሉ ለሀገር የማይጠቅም ስምምነት ሲሉ  ቁርጥ የሆነ ዉሳኔ ላይ ደረሱ።

በመጨረሻም  እንዲህ ሲሉ ለባለቤታቸው ለአፄ ሚኒሊክ  ንዴት፣ ቁጣ  እና ጀግንነት በተሞላበት ስሜት “ይስሙ ንጉሱ!” ይህንን የእናት ሀገሬን ክብር፣ ማንነት እና ጀግንነትን ከሚነካ የውል ስምምነት ጦርነትን እሻለሁ፣ እፋለማለሁ! በሀገሬ ሉዓላዊነት አልደራደርም፤ በማለት ውሳኔያቸውን አስተላለፉ። ከዛም በእሳቸው ንግግር አማካኝነት በምዕራብ በኩል ጎንደር በምስራቅ በኩል አፋር የሚዋስኗት ከደሴ ከተማ 60ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ  ኩራት በሚባል አካባቢ የምትገኘው ቦታ በሚያዚያ 25 ቀን  በ1881 ዓ.ም የዉጫሌ ዉል ስምምነት የተፈራረሙበት ስፍራ ይስማ ንጉስ በሚል መጠሪያ  ተሰየመ፡፡

የውል ስምምነቱን ቁጭ ብለው የተፈራረሙበት ድንጋይ ፅሁፋ እንደነበረበት የታሪክ መዛግብት ይጠቅሳሉ  ነገር ግን አሁን ላይ በዝናብ በውርጭና በፀሀይ ምክንያት ፅሁፉ ባይታይም የይስማ ንጉስ የቱሪስት መዳረሻ ቦታ ዙሪያው በአፀድ ተከቦ ይገኛል እንዲሁም የይስማ ንጉስ ሙዚየም 3.25 በሆነ ሄክታር በ25 ሚሊየን 734ሺህ 720 ብር ከአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በተመደበ ወጪ በሶስት ክፍሎች የተለየ ሙዚየም ተገንብቷል ፡፡

እቴጌ ስለ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ የአይበገሬነት የነጻነት መንፈስና ጀግንነት ያላቸው ሀገራዊ ኩራትና ስሜት አስደናቂ ነው፡፡ የእቴጌ ጀግንነት ነገሮችን ቀድሞ የማወቅ ጥበባቸው፣ ቆራጥ ልበ ሙሉ የሴትነት አቋማቸው ታሪክ የማይሽረው ተምሳሌት ነው፡፡

ከሚያስደንቁት ተግባራቸው እና ንግግራቸው ውስጥ ኮንት አንቶሎኒ  ዉጫሌ  የተዋዋልንበት ወረቀት በፈረንሳዊ ቋንቋ የተፃፈው ይታይ ሲላቸው፡፡ እቴጌ ጣይቱ “እኛ የምናውቀው ባማርኛ የተጣፈውን ነው እንጂ የፈረንሳይ ቋንቋ አናዉቅም አንተ ግን ታውቃለህና ባማርኛ የተፃፈውን እየው” አሉት ከዚህ ወዲያ ኮንት አንቶሎኒ ነገሩ ሁሉ እንዳልሆነለት አይቶ በንዴት ያን የታተመውን ደብዳቤ ቀዳዶ ጣለና “እንግዲህ ፍቅራችን ፈረሰ” ብሎ የጦርነቱን ነገር ገልጦ ተናግሮ ሲወጣ እቴጌ ጣይቱ በረዶ በመሰለ ጥርሳቸው ከትከት ብለው ስቀው “የዛሬም ሳምንት አድርገው በዚህ የሚደነግጥልህ የለም ሂድ የፈከርክበትን አድርግ! እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር ሰጥጦ አገሩን የሚያድን ሰው ከዚህ የሌለ አይምሰልህ፤ የገዛ ደሙን ገብሮ ለገዛ አገሩ መሞት ጌጥ ነው እንጂ ሞት አይባልም አሁንም ሂድ አይምሽብህ የፈከርክበትን በፈቀደህ ጊዜ አድርገው ከዚሁ እንጠብቅሀለን” ብለው የተናገሩት ንግግር ጦርነት የማያስደነግጠው ልበ ሙሉ ጀግንነታቸውን ያስመሰከሩበት አይበገሬ ማንነታቸው የታየበት ንግግር ይገኝበታል።

አፄ ምኒሊክ የኢጣሊያኖቹን የወረራ ሁናቴ ካረጋገጡ በኋላ ዝግጅታቸውን አጠናቀው ከመሳፍንቱና ከመኳንንቱ መክረዉ ዘክረው ከጨረሱ በኋላ  በመስከረም ወር የክተት አዋጅ በይፋ በነጋሪት እንዲህ ሲሉ አወጁ፡፡  “እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ ሀገር አስፍቶ አኖረኝ፡፡ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ  እግዚአብሔር አሳፍሮኛ አያውቅም ወደፊትም ያሳፍረኛል ብየ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም ሀገር የሚያጠፋ ሃይማኖት የሚለዉጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት ሀገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፡፡ ጉልበትም የሌለህ ለልጅህ ለምሽትህ እና ለሃይማኖትህ ስትል በጠሎትህ እርዳኝ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡

አልተውህም ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም፡፡ ዘመቻየም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ” ብለው አወጁ።ይህ ታሪካዊ አዋጅ የኢትዮጵያን አድነት ያረጋገጠ ህዝቡም የንጉሱን ትዕዛዝ በማክበር ለሀገሩ እራሱን አሳልፎ የሰጠበት፣ ካህናቱ የሰምአቱን የቅዱስ ጊዮርጊስን ታቦት ይዘው የዘመቱበት፣ አቅመ ደካሞች በፀሎት የተጉበት፣ ህብረ ብሄራዊ አንድነት የጎላበት፣ በተባበረ ክንድ ድል የተቀዳጀንበት ታሪክ አድርጎታል አደዋ!

በመሆኑም የካቲት 23 ቀን በእለተ እሁድ ከቅዳሴ መልስ የተጀመረው የኢትዮ-ጣሊያን ጦርነት በኢትዮጵያውያን ጀግኖች ድል አድራጊነት የአውሮፓውያንን እጅ አፋቸው ላይ ያስጫነ መላ ጥቁር አፍሪካውያንን በደስታ ጮቤ ያስረገጠ በሀበሻ  ምድር አደዋ ላይ በኢትዮጵያውያን ጀግኖች በዕለተ ሰንበት አመሻሽ  ጀንበር  ስትጠልቅ  በካህናቱ  ውዳሴ፣ በሊቃውንቱ ዝማሬ፣ በምዕመናኑ ሽብሻቦ፣ በአባቶች ቡራኬ፣ በነገስታቱ ምስጋና፣ በማርያም ምለው የጀመሩት ጦርነት በምስጋና ፀሎት የጣሊያን ጦር  ግብዓተ መሬቱ ተፈፀመ፡፡

(በአመለወርቅ መኳንንት)