የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለምን?

ጥር 3/2015 (ዋልታ) በኢትዮጵያ የተመረቱ ምርቶችን ለዓለም ገበያ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ገበያዎች ለማቅረብ “በኢትዮጵያ የተመረተ” እና “በሀገሬ ምርት እኮራለው” የሚሉ መሪ ቃላት የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ልማት ለማስፋፋት ከተጠቀምንባቸው መካከል የሚገኙ ናቸው፡፡ ዘርፉን ለመመገብ ደግሞ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ቅድሚያ የተሰጠው የግብርናው ዘርፍ እንደታሰበው አድጎ ኢንዱስትሪውን መደገፍ ባለመቻሉ የኢንዱስትሪ ዘርፉ በተጠበቀው ደረጃ መራመድ አልቻለም፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ የኮቪድ 19 እና በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተው ጦርነት የኢትዮጵያን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ክፉኛ እንዲዳከም አድርጓል፡፡ ዘርፉን ከዚህ መደብሸት (Stagnation) ለማውጣት መንግስት ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ነው፡፡ ይህ ንቅናቄ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የሚፈልግ በመሆኑ ሁሉም በተሰማራበት ዘርፍ ለተግባራዊነቱ የየራሱን ሚና ካልተወጣ የታለመውን ዕቅድ ለማሳካት አዳጋች ይሆናል፡፡ በመሆኑም የተወጠነውን ውጥን ፍሬያማ ለማድረግና የአገሪቱን ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ሊያፋጥኑ የሚችሉ መንገዶች ላይ ዜጋው የሚከፍለው መስዋዕትነት ለውጤቱ ወሳኝነት አለው፡፡ አሊያም ሃሳቡ በሃሳብነቱ ብቻ ተወስኖ የሚፈለገው ውጤት መምጣት አይችልምና ወደ መሬት ለማውረድ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነትና ተጠያቂነት እንደሚጠበቅበት ልብ ይሏል፡፡

እንደሚታወቀው በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የምጣኔ ሀብት ዕድገት መሠረት በመጣል ታሪኩ የሚወሳዉ የ18ኛው ክፍለ ዘመን የኢንዱስትሪ አብዮት ነው፡፡ አብዮቱ በሰው ጉልበት ላይ የተንጠለጠለውን የግብርናዉን ክፍለ ኢኮኖሚ ወደ መካናይዜሽን በእጅ ከማምረት በፋብሪካ ወደ መታገዝ አገራት እንዲሸጋገሩ እድል ፈጥሮ አልፏል፡፡ዕድሉን አመዛዝነዉ የተጠቀሙ አገራት የምጣኔ ሀብታቸዉን ዕድገት አፋጥነዋል፡፡ የማምረት አቅማቸዉን አሳድገዉ የዉስጥ ፍላጎታቸዉን አሟልተዋል፡፡

የገቢ ምርት እነዲቀንስ ጥራቱን የጠበቀና የተትረፈረፈ ምርት በማምረትና ለዉጭ ገበያ በመላክ ብሎም የወጭ ንግድ ላይ በማተኮርና በመሥራት የተሳካላቸዉ አገራት በዓለም ገበያ ተወዳደሪ መሆን ችለዋል፡፡ የምርታቸዉም ውጤት ካገራቸዉ በወጭ ንግድ  ወደ ሌሎች አገራት ተሻግሮ የአገራቸዉን ስም በማያዉቋቸዉም ሆነ በሚያዉቁት ዘንድ ለማስጠራት ዕድል ሰጥተዋቸዋል፡፡ በዕድገት ማማ ላይ ደርሰዉ ለዜጎቻቸዉም ሰፊ የሥራ እድል እንዲፈጠርና ለታዳጊ አገራት ዜጎች ሥራ ለመፈለግ እንዲሄዱ ከማስገደድ አልፎ ያላዩትን አገር እንዲናፍቁ በማድረግ የአገራቸዉን ልዕልና በሌሎች ዘንድ ገንብተዋል፡፡

ኢትዮጵያም አሁን በያዘችዉ የእድገት ዉጥኗ የአምራች ኢንዱስትሪዉን ምርታማነት ለመጨመርና የማምረት አቅሟን ከፍ በማድረግ በዘርፉ የሚታየዉን ተግዳሮቶችን ለማስወገድና የዜጎቿን የሥራ ዕድል ፍላጎት ለማሟላት አልማ እየሠራች ትገኛለች፡፡

ለዕድገቷ መሰላል በሚሆኑ የወጭ ንግድ ተወዳዳሪነትና የገቢ ምርት በማስቀረት ላይ መሠረት ያደረገና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አድጎ ብልጽግናዋ እዉን እንዲሆን ብሎም ወዳለመችዉ ምዕራፍ ለማድረስ ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአገር አቀፍ ደረጃ ተጀምሮ ገቢራዊ እየሆነ ይገኛል፡፡

ይህ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አገሪቱ በ2022 ዓ.ም እደርሳለሁ ብላ ለወጠነችዉ ዉጥን ስኬትና ለያዘችዉ የብልጽግና ጉዞ እዉን መሆን የሚረዳት መንገድ ሆኖ ተወስዷል፡፡

በተለይ የአምራች እንዱስትሪዉን ወጤታማነት መሠረት ያደረገዉ የንቅናቄዉ ሂደት አድጎ ወደ ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤትነት ተሸጋግሯል፡፡

ለአሥር ዓመታት የሚቀጥለዉ ይህ ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪዉን የማምረት አቅም ከፍ በማድረግ ኢትዮጵያ በዘርፉ ልታስመዘግበዉ የወጠነችዉን ዓላማ የሚያሳካ እንዲሆን ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄዉ የአምራች ኢንዱስትሪዉን ዕድገትና ተወዳዳሪነትን የሚያፋጥን ለዚሁ ስኬት የሚረዱ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ ዉጤታማ አምራቾችን በብዛትና በጥራት ለማፍራትም ያለመ ነዉ፡፡

ለኢንዱስትሪ ግብዓት ለሚሆነዉ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚም ትኩረት ማድረግና ምርታማነትን በመጨመር እንዲሁም ዘርፉ ያጋጠማቸዉን ችግሮች በመፍታት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረከተዉን ድርሻ ከፍ ማድረግ የንቅናቄዉ ትኩረት ነዉ፡፡

የሚሠሩ እጆችን ለሥራ የሚያበቃዉና ለአገር ዕድገት አንዱ ምሶሶ የሆነዉን የአምራች ኢንዱስተሪ ዘርፍ ዉጤታማ ለማድረግም ችግሮች ተለይተዋል፤ የመፍትሄ አቅጣጫዎችም ተተልመዉለታል፡፡

ባለፉት ዓመታት የዓለም ስጋት የሆነዉ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአምራች ኢንዱስትሪዉ ዘርፍ ያደረሰዉ መቀዛቀዝና ዘርፉ የሚጠይቀዉን ድጋፍ በሚጠበቀዉ መልኩ ተደራሽ አለማድረግ የባለድርሻዎች ቅንጅታዊ አሠራር ጉድለት እንዲሁም የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ማነስና ሌሎች ተግዳሮቶች በንቅናቄ ሂደት መፍትሔ ለማበጀት ተለይተዋል፡፡

እነዚህና ሌሎች ለአምራች ኢንዱስትሪ ዕድገት ማነቆ የሆኑ ተጓዳኝ ችግሮችን በመፍታት የማምረት አቅም በማሳደግና አምራቾችን በማበረታታት እንዲሁም አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ወደ ሥራ በማስገባት ዘርፉን ምርታማ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠራባቸዉም ተወስደዋል፡፡

የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነትን በማሳደግና ተወዳዳሪ በማድረግ በቂ ምርት ለዓለም ገበያ በማቅረብ ወጪ ንግዱን ከፍ በማድረግ እንዲሁም የገቢ ምርት ንግድ በመቀነስና በማስቀረት የውጭ ምንዛሪ ላይ ጥገኛ ከመሆን ማላቀቅ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አንዱ ዓላማ ነዉ፡፡

በዚሁ በተያዘዉ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአጭር ጊዜ ዉስጥ የአምራች ኢንዱስትሪ ድርሻን በጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ድርሻ  ከነበረበት 6.8 ከመቶ ወደ 17.8 ከመቶ ለማሳደግና ለአምስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠርም ታቅዷል፡፡

ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዉጤታማነት የባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ መሆኑም በንቅናቄዉ ሂደት ትኩረት የተሰጠበት ነው፡፡ ለአምራች ኢንዱስትሪዉ ምርታማነት ቅልጥፍና መንገድ የሚቀይሱ የአሠራር ሥርዓቶችን ማዘመን መሠረተ ልማቶችን ተደራሽ ማድረግ ለሥራ ስኬታማነት ትኩረት መስጠት ብሎም ለተቋማዊ ሽግግር አበክሮ መስራት ትኩረት የሚሹ ዐበይት ጉዳዮች ናቸዉ፡፡ በተለይ የቦታ ዝግጅት፣ ብድር ማመቻቸትና በጊዜ ማቅረብ መብራትና ዉሃ ማሟላት ከመንግስትና ከባለድርሻ አካላት ይጠበቃሉ፡፡

የተፈጠሩ መልካም አጋጣሚዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ዉጤታማ ለመሆን መትጋትና በጥራትና በብዛት በማምረት በአገርና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ በመሆን አገሪቱ የምትጠብቀዉን ዓለማ ማሳካት ደግሞ የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶችና የኢንተርፕራይዞች ድርሻ ይሆናል፡፡

ዜጋዉ ደግሞ ኢትዮጵያ ስታመርትና የዉጤታማነት ጉዟዋን ስትጀምር የኢትዮጵያ ምርት በኢትዮጵያዊያን በሚል እሳቤ ሲሸመትና በአገሬዉ ምርት ሲጠቀምና ሲኮራ ከወጭ ለሚመጣዉ ዓይኑን ከማማተር በአገሩ የዉስጥ ምርት ላይ ሲያተኩር ያኔ የኢትዮጵያ ታምርት ንቀናቄ ተልዕኮዉን ያሳካል፡፡ ለዘህም ስኬት በተለይ ወጣቱ ትዉልድ በዘርፉ በመሠማራት ለውጤታማነቱ በመትጋትና የራሱን ምርት በመጠቀም በራስ መተማመንን በመገንባት ረገድ ድርሻዉ ከፍተኛ በመሆኑ የሀገር ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡

በዚህ ረገድ የራሳቸዉን ምርት በመጠቀም ለውጥ ያመጡ አገራት እንደ ቻይና፣ ህንድና ሲንጋፖር በማደግ ላይ ላለን ለኛ እንደምሳሌ የሚጠቀሱ አገራት ናቸዉ፡፡ ለዚህም ዜጋዉ የራሱን ምርት በመጠቀም ምን ያህል ለአገሩ ዕድገት እንደሚቆረቆር ማየት ይቻላልና እኛም ምርታችንን በመጠቀም ድርሻችን እንወጣ፡፡

ለኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሂደት የአምራች ኢንዱስተሪዎች መዋቅራዊ ሽግግር ማድረግ ለዚህ ስኬት ደግሞ የተጠናከረ የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ አሠራር እንደሚያስፈልግ እሙን ነዉና ሁሉም በየዘርፉ ኃፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡

የአምራች አንዱስትሪ ዳብሮ የጥሬ እቃ አቅራቢዉ ግብርናዉ ተመንድጎ ሲታይና ምርት ተተርፍርፎ በአገራችን ምርት የምንጠቀምበት ጊዜ እዉን ሲሆን ወደ ገቢ ምርቶች ማማተር ያቆማል፡፡ የአገር ውስጥ ምርት ወደ ዓለም ገበያ በመግባትም ተወዳዳሪ ሆኖ ባንዲራችንን ከፍ አድርጎ በገበያ ያዉለበልባል፡፡ የዛኔ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዉጤት እንቋደሣለን፡፡

ቸር እንሰንብት፡፡

 

በሠራዊት ሸሎ