የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ተመረቀ

የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል

ጥር 3/2015 (ዋልታ) በአዲስ አበባ የተገነባው የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ተጠናቆ ተመረቀ።

ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የሚገኙት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማኅማት ማዕከሉን መርቀውታል።

የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል በቻይና መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተገንብቶ የተጠናቀቀ ሲሆን ማዕከሉ በ40 ሺሕ ስኩዌር ሜትር ላይ ያረፈና የተቋሙን ሥራ ለማሣለጥ የሚያስችሉ ዘመናዊ ቁሳቁስ መሟላቱ ተጠቁሟል።

ጎን ለጎንም የድንገተኛ ክፍል፣ የመረጃ ክፍል፣ ላብራቶሪ፣ የሥልጠና እና የመሰብሰቢያ አዳራሽና ሌሎች መሠረታዊ ክፍሎችን የያዘ ነው ተብሏል።

ማዕከሉ የአህጉሪቱን የበሽታ መከላከል ሥራ በተለይም በአፍሪካ አስተማማኝና ዘላቂ የጤና ሥርዓት ለመዘርጋት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ታምኖበታል።

የማዕከሉ ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ ማለትም አገልግሎት ለማስጀመር የሚያስችሉ የማጠቃለያ ሥራዎች እየተካሄደ ሲሆን በቅርቡ ተጠናቆ ማዕከሉ ወደ ሥራ ይገባል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።

የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል የተገነባው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2018 የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ በገቡት ቃል መሠረት ነው።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW