ግንቦት 14/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ለፈጠራ ስራዎች ሙሉ ግብዓት ማቅረብ የምትችል ሀገር ናት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ11 ክልሎችና 2 ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የፈጠራ ባለሙያዎች የሚያሳትፈው 3ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ለፈጠራ ስራዎች ሙሉ ግብዓት ማቅረብ የምትችል ሀገር መሆኗን ጠቅሰው የቴክኖሎጂ ግብዓቶቹ ከግብርናው፣ ከኢንዱስትሪና መሰል ሴክተሮች ጋር የተሳሰሩ ባለመሆናቸው ተፈላጊው ውጤት አልተመዘገበም ብለዋል።
በስራና ክህሎት ሚኒስቴር የቀረበውና ለቀጣይ 4 ቀናት የሚካሄደው የክህሎት ውድድር ግብዓቶችን ማስተሳሰርን ዓላማ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡
የክህሎት ውድድሩ በስልጠና ማዕከላት የተዘጋጁ፣ በልዩ የቴክኖሎጂ ስራ የበለፀጉና ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን የሚያሳትፍ መሆኑ ተጠቁሟል።
በደረሰ አማረ