በኢትዮጵያ የኢኮኖሚውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ገበያ መር የሰው ኃይልና የክህሎት ልማት ሪፎርም ተደርጓል – የስራና ክህሎት ሚኒስቴር

ሙፈሪሃት ካሚል

ግንቦት 12/2015 (ዋልታ) በኢትዮጵያ የኢኮኖሚውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ገበያ መር የሰው ኃይልና የክህሎት ልማት ሪፎርም በማድረግ ውጤታማ ስራ መከናወኑን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው በ2025 ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የፌደራል መንግስት ተቋማት የዘጠኝ ወር የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ተገምግሟል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በኢትዮጵያ የሰው ኃይል እና የክህሎት ልማት ሥራ ገበያ መር እንዲሆን የሚያስችል ሪፎርም መደረጉን ገልጸው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ100 በላይ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መንገድ የክህሎት ስልጠና እንዲሰጡ በማደራጀት የለውጡን እሳቤዎች ገቢራዊ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

የክህሎት ስልጠናው የገበያውንና የኢኮኖሚውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ በዚህም በዘጠኝ ወራት ብቻ ለሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም የፋይናንስ አቅርቦት፣ የመስሪያና የመሸጫ ቦታዎችን በተመለከተ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚ እንዲሁም ኢኖቬሽንና ምርምር ዘርፎች እመርታ እያሳየች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብዙ አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል አሰራር እየገቡ በመሆናቸው የግልም ሆነ የመንግስት ተቋማት በዲጂታል ኢኮኖሚ ውጤት እያስመዘገቡ ነው ብለዋል፡፡

የሚኒስቴሩ የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም በ2025 ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያስችል መሆኑ መገምገሙን ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኢኖቬሽንና ምርምር ዘርፍም የሥራ ፈጣሪዎችን አቅም ለማጎልበት የሚያስችል ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ ስራዎችን የሚያቀላጥፉ የፖሊሲና የህግ ማዕቀፎች እንዲዘጋጁ በማድረግ ዘርፉን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡