ኢትዮጵያ በሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት የሥርዓተ ምግብ ጉባኤ የነበራት ተሳትፎ ስኬታማ ነው – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

ሐምሌ 19/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያ በሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት የሥርዓተ ምግብ ጉባኤ የነበራት ተሳትፎ ስኬታማ መሆኑን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ እንዳሉት በግብርናው ዘርፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ውጤታማ እንቅስቃሴዎችን የሚያሳዩ ልምዶች በጉበኤው ቀርበዋል።

በጉባኤው የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ግብርናን በማዘመን የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥና በሥርዓተ ምግብ ሽግግር ለማምጣት እየወሰደች ባለው የፖሊሲ እርምጃ ውጤቶች ዙሪያ ገለጻ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የኩታ ገጠም እርሻን በማስፋፋት፣ ለየስነ ምህዳሩ ተስማሚ የሆኑ የተሻሻሉ ዝርያዎችን፣ አነስተኛ ቴክኖሎጂዎችንና ሌሎች ግብአቶችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለኢኮኖሚው ዕድገት የላቀ አበርክቶ እንዲኖረው እየሰራች መሆኑን አንስተዋል ነው ያሉት።

አያይዘውም በአረንጓዴ አሻራ፣ በበጋ መስኖ በተለይም በበጋ ስንዴ ምርት እና በሌማት ትሩፋት እየተገኙ ያሉ ውጤቶችን ለጉባኤው ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግብርና ዘርፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የስራ እድል ፈጠራን ለማበረታታትም ሆነ የስርዓተ ምግብ ሽግግር ለማድረግ አዲስና የተለየ የፋይናንስ ሞዴል ያስፋልጋል በማለት በአጽንኦት መናገራቸውንም እንዲሁ።

በአንደኛው ጉባኤ የተቀመጡ ዘላቂና አካታች የስርዓተ ምግብ ሽግግር አቅጣጫዎች ጥሩ አፈጻጸም የታየባቸው ቢሆንም በፋይናንስ አቅርቦት፣ በዓለም አቀፍ ትብብር፣ በአየር ንብረት ለውጥና በሰው ሰራሽ ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቋቋም በትብብር በመስራት በኩል በርካታ ችግሮች መስተዋላቸውን አንስተዋል ብለዋል።

በመሆኑም ሀገሮች በስርዓተ ምግብ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ በአነስተኛ እርሻ ስር ነቀል ለውጥ በማምጣት ሽግግሩን ማፈጣን እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፅንኦት ማንሳታቸውንም ተናግረዋል።

ለዚህም የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎን እንዲያሳድጉና ለግብርና ቴክኖሎጂ መስፋፋት እንዲሰሩ ጠይቀዋል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር በሰበሰቡት ዓለም አቀፍ የልማትና የፍልሰት ኮንፈረንስ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባደረጉት ንግግር፣ ሀገራዊ ዕድገትን ማፋጠን የስራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋፋትና ድህነትን ለማቃለል፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ፍልሰትን ለመቀነስ ወሳኝ እንደሆነ አንስተዋል።

እንዲሁም የፍልሰት መነሻ ምክንያቶችን ለይቶ ለመቅረፍ፣ ለስራ ዕድል ፈጠራ አዳዲስ የፋይናንስ ስርአት መዘርጋትና የክህሎት ግንባታን ማዕከል ያደረገ የስራ ስምሪት መተግበር እንደሚገባም መናገራቸውን ጠቅሰዋል።

በሌላ መልኩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጣሊያን ቆይታቸው በሮም ከተማ ለጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ ያስቀመጡት ምሰለ ቅርጽ ኢትዮጵያ ጀግኖቿንና ታሪኳን ለዓለም ለማስተዋወቅ እድል የፈጠረ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በጉባኤው የተገኙት የግብርና እና የፕላንና ልማት ሚኒስትሮች በአንደኛው የተባበሩት መንግስታት የስርዓተ ምግብ ጉበኤ የተቀመጡ አቅጣጫዎች አፈፃፀም፣ በተገኙ ውጤቶችና ተግዳሮች ላይ የኢትዮጵያን የስራ እንቅስቃሴ ሪፖርት ማቅረባቸውን ተናገረዋል።

ዘላቂና አካታች የስርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማሳካት በሚደረገው እንቅስቃሴ በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጅ፣ በአመራር፣ በአየር ንብረት ለውጥ ማላመድ ዙሪያ ያሉ የኢትዮጵያ ልምዶች መቅረባቸውንም ገልጸዋል።

በየመድረኮቹ በነበሩ ውይይቶች ኢትዮጵያ በሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ደምቃ ሰንብታላች።

ከዚህ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ልኡክ ከበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በማህበረ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ውጤታማ ውይይቶችን እንዳደረጉ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።